ቀጥታ፡

በበጀት ዓመቱ 810 ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በተያዘው በጀት ዓመት 810 ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከሲዳማ፣ ደቡብና ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ለተውጣጡ አመራሮች የቡና ጥራት ንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ አካሂዷል።

በባለስልጣኑ የቡና ሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍቃዱ ደፈረሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከቡና ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

ብራዚል ለአለም ገበያ በምታቀርበው የቡና መጠን ላይ 20 በመቶ በመጨመር ማቅረብ መጀመሯን ጠቁመው ይህም የቡና ዋጋ ዝቅ እንዲል የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራችን ጥራት ያለውን ቡና በማቅረብ ገቢዋን ከፍ ማድረግ እንዳለባት የተናገሩት አቶ ፍቃዱ፤ በቡና ገበያው ጥራት ያለው ቡና እየቀረበ እንደሆነ ተናግረዋል።

የቡናው ደረጃ አንደኛ እንዲሆን እየተሰራ እንደሚገኝም ነው አቶ ፍቃዱ የገለጹት።

ባለፈው ዓመት በጀት ዓመት 652 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል።

በተያዘው በጀት ወደ ውጭ የሚላከውን የቡና መጠን 810 ሺህ ቶን በማድረስ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ግብ መጣሉን ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር በበኩላቸው ክልሉ ባለፈው በጀት ዓመት ቡና በማቅረብ ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረው አስታውሰዋል።

የቡና አቅርቦትንና ጥራትን ከፍ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ክልሉ 48 ሺህ 498 ቶን ቡና ለማቅረብ አቅዶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 3 ሺህ 231 ቶን የታጠበና ደረቅ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ተናግረዋል።

ለውጭ የሚቀርበውን ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አርሶ አደሩ ድረስ ክትትል የሚያደርግ ግብረ-ሃይል መኖሩን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ሀጢሶ ጠቁመዋል።

ክልሉ በበጀት ዓመቱ 30 ሺህ ቶን የታጠበና ደረቅ ቡና ለገበያ ለማቅረብ ማቀዱን አመልክተዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ መስፍን ቃሬ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከዘር ዝግጅት ጀምሮ የቡና ጥራትን ለማሳደግ መሰራቱን ጠቅሰዋል።

የቡና ጥራትና መጠንን ማሳደግ ጎን ለጎን መሰራት እንዳለበት የተናገሩት አቶ መስፍን፤ ህገ-ወጥ የቡና ምርት ዝውውርን የመከላከል ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም