የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊዮን ብር መድቧል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊዮን ብር መድቧል
ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊዮን ብር መመደቡን አስታወቀ።
የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ አያሌው እንደገለጹት ባንኩ ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ስራ ፈጣሪ ወጣቶች በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋማት ለሀገር የሚጠቅሙ አዳዲስ የፈጠራ ሀሳቦችን እውን ለማድረግ በቂ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
መንግስት የፈጠራ ባለቤቶች ሃሳባቸውን ወደ ተግባር እንዲቀይሩ የተለያዩ አሰራሮችን እየዘረጋ ቢሆንም፤ የፋይናንስ ተቋማት ለጀማሪ የፈጠራ ባለቤቶች የሚያደርጉት ድጋፍ መጠነኛ መሆኑ ይነሳል።
በቴክኖሎጂ የታገዙ መፍትሄዎችን የሚሰጥ ድርጅት ያቋቋመው ወጣት ዳግማዊ በድሉ፤ እንደ ሀገር ጀማሪ የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ከሚገጥሟቸው ችግሮች አንዱና ዋነኛው የገንዘብ እጥረት መሆኑን ያነሳል።
በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የፈጠራና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል መግባት በመቻላቸው የተለያዩ ድጋፎችን እያገኙ መሆኑን ተናግሯል።
የእነሱ ተቋም ዕድለኛ ሆኖ በማዕከሉ ስልጠናዎችን ቢያገኝም፤ በርካታ የፈጠራ ባለቤቶች ይህን እድል ስለማያገኙ ሃሳባቸውን ወደስራ ለመቀየር ይቸገራሉ ብሏል።
ባህላዊ የቤት ማስዋቢያዎችን በመስራት የተሰማራችው ፌቨን ኤልያስ እንደተናገረችው የተደረገውን ምርጫ በማለፍ የማዕከሉ ተጠቃሚ በመሆኗ የአይነት ድጋፎችን እያገኘች ነው።
የፈጠራ ሃሳብ ባለቤቶች ስራቸውን ወደ ተግባር እንዳይቀይሩ ማነቆ የሆነባቸውን የገንዘብ አቅርቦት ለመፍታት የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልፃለች።
የሀገርና የማህበረሰብ ችግሮችን መነሻ በማድረግ መፍትሔ ይዘው የሚመጡ የፈጠራ ሀሳቦች ሀገርን ስለሚጠቅሙ በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ በማመላከት።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው በበኩላቸው ባንኩ ስራ ፈጣሪዎችን ለመደገፍ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ሃሳብ ይዞ የሚመጣ ስራ ፈጣሪ ፈጠራው የራሱ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ፤ የፈጠራ ሃሳቡ አዋጭ መሆኑን በማጥናት ወጪውን ሸፍኖ ሃሳቡ ወደስራ እንዲቀየር ድጋፍ እንደሚያደርግም ነው የገለፁት።
እስካሁን ባለው በግብርናው ዘርፍ የመጡ የፈጠራ ሃሳቦች የአዋጭነት ጥናት አጥንተው የቢዝነስ እቅድ እንዲያቀርቡ እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
ባንኩ የፈጠራ ባለቤቶችን ለመደገፍ 4 ቢሊዮን ብር መመደቡንና የባንኩን ድጋፍ የሚሹ ስራ ፈጣሪዎች በስፋት ከመጡ በጀቱን ከዚህም በላይ ከፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የግል ዘርፉ በዲጂታል ኢኮኖሚው መሳተፍ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ነው።