ቀጥታ፡

በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ለተሰማሩ አካላት በአነስተኛ ወለድ የብድር አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍና በአነስተኛ ወለድ የብድር አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት በግብርና ሚኒስቴር እና በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት መካከል ተፈረመ።

ከጣልያን መንግስት በተገኘ የ10 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ስራ ላይ ለማዋል ስምምነት የተደረገበት ይህ ፕሮጀክት በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካለት ብድር ለማመቻቸት የሚያስችል ነው ተብሏል።

ስምምነቱን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን በኢትዮጵያ የተመድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር አዉራሊያ ፓትሪዚያ ካላብሮ ጋር ተፈራርመዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ለቡና ላኪዎች፣ አቅራቢዎችና አምራቾች የፋይናንስ ውስነንት ዋነኛ ማነቆ መሆኑን ጠቅሰው ዛሬ የተደረገው የቴክኒክና የገንዘብ ትብብር ስምምነት ችግሩን ያቃልለዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የተመድ ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር አዉራሊያ ፓትሪዚያ ካላብሮ በበኩላቸው ትብብሩ በቡና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትን በመለየት ድጋፍ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ፕሮጀክቱ በቡና ዘርፍ ላይ በሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ስጋትን የሚቀንስ የአጋርነት ሞዴል መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የቡና መጠን፣ ጥራት እና ዋጋ ለማሳደግ በአነስተኛ ወለድ የብድር አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የግብርና ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም