የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዙሪክ በረራ መጀመሩ በአፍሪካና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዙሪክ በረራ መጀመሩ በአፍሪካና አውሮፓ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል
ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በረራ መጀመሩ በአፍሪካና አውሮፓ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2015 ዓም ወደ ስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በረራ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው እንዳሉት፤ አየር መንገዱ በስዊዘርላንድ ከጄኔቭ ቀጥሎ ሁለተኛ መዳረሻው መሆኑን ገልጸዋል።
ከዙሪክ በተጨማሪ ወደ ዚምባቡዌ ቡላዋዮ በረራ በመጀመር በሀገሪቱ መዳረሻውን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።
ሁለት መዳረሻዎችን በአንድ ቀን ማስጀመር ለየት ያደርገዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፤ በዙሪክ እና በቡላዋዩ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል።
በዚህም የዙሪክ በሪራ መጀመር የአውሮፓ መዳረሻውን 19 ማድረሱን ጠቁመው የሁለቱን አገራትን ህዝቦች ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና በቱሪዝም ዘርፍ የበለጠ ያስተሳስራል ብለዋል።
የዚምባቡዌ የኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው የቡላዋዮ ከተማ በረራ መጀመሩ የሁለቱ አገራት የዲፕሎማሲ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የበለጠ ያጠናክረዋል ነው ያሉት።
አየር መንገዱ በአፍሪካ የመዳረሻዎቹ ብዛት ወደ 63 ከፍ ማለቱን በመጠቆም።
አቶ መስፍን አክለውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በረራ መጀመሩ በአፍሪካና አውሮፓ መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።
አየር መንገዱ አገራትን ከአገራት እያስተሳሰረ የኢትዮጵያ መለያ፣ የአፍሪካ ኩራት የዓለም ድልድይ መሆኑንም ገልጸዋል።
አየር መንገዱ መዳራሻዎቹን ለማስፋት የሚያስችል ተጨማሪ አውሮፕላኖችን ለማስመጣት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የስዊዘርላንድ ኤምባሲ ምክትል የሚሲዮን መሪ ኦሊቨር ኦሄን በበኩላቸው የአየር መንገዱ ወደ ዙሪክ በረራ መጀመር የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ያጠናክራል ብለዋል።