የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲዊዘርላንድ ዙሪክ እና ዙምባቡዌ ቡላዋዮ ከተሞች በረራ ጀመረ

ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሲዊዘርላንድ ዙሪክ እና ዙምባቡዌ ቡላዋዮ ከተሞች በረራ በዛሬው ዕለት ጀምሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው እንዳሉት ወደ ዙሪክ የሚደረገው በረራ በሲዊዘርላንድ ከጄኔቭ ቀጥሎ ሁለተኛ መዳረሻው ነው።

አየር መንገዱ ከሲዊዘርላንድ በተጨማሪ ወደ ዙምባቡዌ ቡላዋዩ ከተማ በረራ መጀመሩን ተከትሎ በዙምባቡዌ ያለውን የበረራ መዳረሻ ብዛት ሶስት አድርሷል።

አየር መንገዱ ወደ ሁለቱ ከተሞች የጀመረውን አዲስ በረራ በአንድ ቀን ማስጀመሩ ለየት ያደርገዋል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ወደ ዙሪክ የሚደረገው በረራ በሳምንት ሶስት ግዜ መሆኑን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ የዙሪክ በረራ መጀመሩን ተከትሎ በአውሮፓ ያለውን የበረራ መዳረሻ ብዛት 19 የቡላዋዮ አዲስ በረራ መጀመሩ ደግሞ በአፍሪካ ከተሞች ያለውን መዳረሻ ብዛት 63 እንዳደረሰለት ተገልጿል።

ትላንት በተከናወነው የበረራ ማስጀመር መረሃ-ግብር ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ፣ በኢትዮጵያ የሲዊዘርላንድ ኢምባሲ ምክትል ሚሽን ኦሊቨር ኦሄን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም