የዲጂታል ባንኪንግ፣ የሰው ኃይልና ካፒታልን በማጠናከር ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ አቅም መፍጠር ይገባል- የባንክ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ባንኪንግ፣ የሰው ኃይልና ካፒታልን በማጠናከር ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ አቅም መፍጠር ይገባል- የባንክ አመራሮች
ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ) በዲጂታል ባንኪንግ የተጀመሩ ለውጦችን በሰው ኃይልና በካፒታል በማጠናከር በቀጣይ ወደ ሀገር ውስጥ ከሚገቡ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ የሚያደርግ አቅም መፍጠር እንደሚገባ የባንክ አመራሮች ተናገሩ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ሙዓለ ንዋይ አፍሳሾች ክፍት የሚያደርገው ፖሊሲ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑ የሚታወስ ነው።
መንግሥት የውጭ ሀገር ባንኮች ወደ ሀገሪቱ በመግባት በፋይናንስ ዘርፉ ላይ እንዲሳተፉ መፍቀዱን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር ውስጥ የባንክ አመራሮች፤ ብዙ ልምድ ይዘው ከሚመጡ የውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ እና ተመራጭ ለመሆን ጠንካራ ዝግጅት ያስፈልጋል ብለዋል።
የህብረት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ከበደ፤ የባንክ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለውጭ ሀገራት የዘርፉ ባለሀብቶች ዕድል መሰጠቱ በርካታ ጠቀሜታዎች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ የማግኘት ዕድልን ማስፋት እና የውድድር መድረክን መፍጠር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በቀጣይም ባንኮች በገበያው ላይ ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅንጅት መስራት ይኖርብናል ነው ያሉት።
የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ልዑልሰገድ ንጉሴ በበኩላቸው፤ የውጭ ሀገር ባንኮች በኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ እንዲቀላቀሉ መወሰኑ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል።
በተለይም በቴክኖሎጂው መስክ ከፍተኛ ዕውቀት ይዘው ስለሚመጡ ለዕውቀት ሽግግር ምቹነቱን በማንሳት፤ የኢትዮጵያ ባንኮችም የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ትምህርት እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
አቶ ልዑልሰገድ አክለውም፤ ከውጭ ባንኮች ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችለንን ጠንካራ የካፒታል አቅም ማጎልበት አለብን ብለዋል።
በዲጂታል ባንኪንግ የተጀመሩ ለውጦችን በሌሎች ዘርፎችም ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአማራ ባንክ የገበያና የኢኮኖሚ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ወልዴ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ባንኮችን መቆጣጠር የሚያስችለውን አቅም ከወዲሁ ማሳደግ አለበት።
የሰው ኃይል አቅማችንን ማሳደግና የሚመጣውን የውድድር ጫና ለመቋቋም በቂ ዝግጅት ማድረግ ለነገ የማይባል ስራ ነው ብለዋል።