ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚዘክርና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ሰልፍ በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሔድ ነው

ጥቅምት 21/ 2015 (ኢዜአ ) አሸባሪው ሕወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ ሁለተኛ ዓመት የሚዘከርበትና የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በዋሺንግተን ዲሲ የፊታችን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ።

ሰልፉ መነሻውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መድረሻውን የአሜሪካ መንግስት መቀመጫ ወደ ሆነው ‘ካፒቶል ሂል’ በማድረግ እንደሚከናወን ተገልጿል።

በሰልፉ ላይ አሸባሪው ሕወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንደሚዘከር የሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዋሺንግተን ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ጣሰው መላከሕይወት ለኢዜአ ገልጸዋል።

አገር መከላከያ ሰራዊት በሽብር ቡድኑ ላይ ያስመዘገባቸው ድሎች እንደሚከበሩም አመልክተዋል።

ሰልፈኞቹ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚያደርጉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙና አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን እንድትቆም የሚጠይቁ መፈክሮችን ያሰማሉ ብለዋል።

በሰልፉ ላይ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ይሳተፉበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሕዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች “ለአገራዊ ጥሪ ወገናዊ ምላሽ” በሚል መሪ ሀሳብ የገቢ ማሰባሳቢያ መርሐ-ግብር በዋሺንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ነው አቶ ጣሰው የገለጹት።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ለሃገራቸው የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል።

የፊታችን ሐሙስ የሚካሄደውን ሰልፍ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር ዲሲ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት፣ከተለያዩ ተቋማትና አገር ወዳዶች ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም