ቀጥታ፡

የአዲስ አበባን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረጉ ማናቸውንም ሙከራዎች በብቃት መከላከል የሚችል የፖሊስ ኃይል ተገንብቷል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጥቅምት 20/2015 /ኢዜአ/ የአዲስ አበባንና ነዋሪዎቿን ሰላም ለማደፍረስ የሚደረጉ ማናቸውንም ሙከራዎች በብቃት መከላከልና ማክሸፍ የሚችል የፖሊስ ኃይል መገንባቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።

ከንቲባዋ ይህን ያሉት የአዲስ አበባ ፓሊስ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የጸጥታ አካላት ላከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት እውቅና እና ሽልማት በሰጠበት ወቅት ነው።

የተሰጣቸውን ተልዕኮ  በብቃት የተወጡና የላቀ የስራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ እንዲሁም የህይወት መስዋትነት ለከፈሉ ቤተሰቦች የምስጋና የምስክር ወረቀትና ሌሎች ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤም በሰጡት  ቁርጠኛ አመራር እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት፤ ከተማ አስተዳደሩ በቴክኖሎጂ የዘመነና ጠንካራ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

የጸጥታ ኃይሉ ከተማዋን የሽብር ማዕከል ለማድረግ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማክሸፍ ከከተማዋ ነዋሪ ጋር አኩሪ ተግባር ማከናወኑን ጠቅሰው ለዚህም እውቅና ይገባዋል ብለዋል።

ከንቲባዋ "ኢትዮጵያ ጸንታ ዛሬ ላይ የደረሰችው ህይወታቸውን ሳይሰስቱ ሁሌም መስዋትነት የሚከፍሉላት ጀግኖች ልጆች ስላሏት ነው"  ብለዋል ከንቲባዋ።

በቀጣይም የፖሊሲ ኃይልን በማዘመን፣ በስነምግባር የታነጸና በህዝብ ዘንድ ከበሬታን በማትረፍ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር በትጋት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በበኩላቸው የህወሃት የሽብር ቡድንና ሌሎች የሽብር ቡድኖች የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማወክ ያደረጉት ሙከራ  በጸጥታ ኃይሉ ብቃት መክሸፋቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በተጨማሪም የተደራጁ ወንጀሎችን በፖሊሳዊ ጥበብና በጥናት ላይ ተመስርቶ በተሰራው ስራ የህይወት፣ የአካልና የንብረት ውድመት ሊፈጸሙ የነበሩ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል።

የዛሬው እውቅና የከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች እስከ ህይወት መስዋትነት በመክፈል ያበረከቱትን አስተዋፅኦ ታሳቢ ማድረጉን ገልጸው በቀጣይም ለላቀ ተልዕኮ የምንዘጋጅበት ነው ብለዋል።

የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፌደራል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን  የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በከተማዋ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ሲዘዋወሩ የነበሩ ከፍተኛ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በትብብር  መያዙን አውስተዋል።

በቀጣይ የሀገሪቱንና የመዲናዋን ሰላም በማስጠበቅና እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከናወኑ የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን  አክለዋል።

ተልዕኳቸውን በብቃት በመፈጸም እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ኢንስፔክተር ደሞዝ በሪሁንና ኮማንደር ትግስት ኃይሉ እውቅናው ተልዕኳቸውን በትጋት የበለጠ እንዲሰሩ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም