ቀጥታ፡

የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጫናና የውጭ ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በጄኔቫና በለንደን ሊካሔድ ነው

ጥቅምት 20/ 2015 (ኢዜአ) አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በጄኔቫና ለንደን ከተሞች በቀጣዩ ሳምንት ይካሄዳል።

ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በጄኔቫ በሚካሄደው ሰልፍ መቀመጫውን በስዊትዘርላንድ ያደረገው የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሀኖም አሸባሪው ህወሃትን በመደገፍ የሚያካሒደውን ጸረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ድርጅቱ እንዲያስቆም ሰልፈኞቹ ድምጻቸውን ያሰማሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ሊከተለው የሚገባውን የገለልተኛነት መርሆ በመጣስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ በመግባት ጫና ለመፍጠር የመደረገውን ጥረት በጽኑ እንደሚያወግዙም ኢዜአ ከ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክፎርስ ኢሮፕ’ እና ከሰልፉ አዘጋጅ ኮሚቴዎች ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በጄኔቫ መቀመጫውን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምደው ኃላፊነት እና ሚዛናዊነት የጎደለው አቋም እንዲታረም የሚያሳስቡ መፈክሮች እንደሚሰሙም ገልጿል።“ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በመጋፋት የሚያደርጉትን ጫናና ጣልቃ ገብነት አንቀበልም” የሚሉ መልዕክቶችም እንደሚስተጋቡ ተነግሯል።

ሰልፉ ኢትዮጵያዊያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለኢትዮጵያ ሕልውና ፣ሉዓላዊነትና አንድነት ምንጊዜም ዘብ እንደሚቆሙና ለኢትዮጵያ ድምጽ መሆናቸውን የሚያሳዩበት እንደሆነ ነው ከሰልፉ አስተባባሪዎች የተገኘው መረጃ የሚያመለክተው።

በተያያዘ ዜናም ይሄንኑ አላማ የተከተለና የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም በለንደን በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ፊት ለፊት ይካሄዳል።

May be an image of 4 people and text that says 'I stand with Ethiopia #NoMore Rally London AMERICAN EMBASSY 9 ELMS LONDON SW11 7US DATE 6 NOVEMBER 2022 TIME: 2-6PM ምን ክብር አለኝን ከህገሬ በላይ!! #No More #NoMore Proxy war #NoMore Sanction #NoMore Political Pressure #NoMore TPLF #DisarmTPLF #Support Ethiopia stand with Ethiopia Organiser: Defend Ethiopia UK Contact: defendethiopiauk@gmail.com'

“የውክልና ጦርነት እናወግዛለን፣ሕወሓት ሽብርተኛ ቡድን ነው፣ሕወሓት ትጥቁ ይፍታ፣ኢትዮጵያን ደግፉ፣የፖለቲካ ጫና አንቀበልም እና ከኢትዮጵያ ጎን እቆማለሁ” የሚሉ መፈክሮች በሰልፉ ላይ እንደሚሰሙ ተገልጿል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት በኢትዮጵያ ሁኔታ ፍትሐዊና ሚዛናዊ አተያይ እንዲኖረው የሚያሳስቡ መልዕክቶች እንደሚተላለፉም ተጠቅሷል።ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ሰልፎች በቀጣይ በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ለማካሄድ እቅድ መያዙን ‘ዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክፎርስ ኢሮፕ’ አስታውቋል።

ቀደም ሲልም ተመሳሳይ ይዘት ያለውና አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነትና ጫና የሚቃወም ሰልፍ ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም በቤልጂየም ብራሰልስ የአውሮፓ ኮሚሽን ፊት ለፊት መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም