ቀጥታ፡

አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በመዲናዋ መከፈቱ ያለንን እውቀት የምናጎለብትበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል- ተጠቃሚዎች

ጥቅምት 20 ቀን 2015 (ኢዜአ)  አብርሆት ቤተ መጻሕፍት በመዲናዋ መከፈቱ ያለንን እውቀት የምናጎለብትን ምቹ ሁኔታን ፍጥሮልናል ሲሉ የቤተ መጻሕፍቱ ተጠቃሚዎች ገለፁ፡፡

ቤተ መጻሕፍቱ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጥ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአብርሆት ዳይሬክተር ተናግረዋል።

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በይፋ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የቤተ መጻሕፍቱን አገልግሎት አሰጣጥ በቦታው በመገኘት ቅኝት በማድረግ ተጠቃሚዎችንና የቤተ መጻሕፍቱን ኃላፊዎች አነጋግሯል።

ከተጠቃሚዎች መካከል አቶ ደጀኔ ወልደጨርቆስ ያላቸውን እውቀት እና ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ለማንበብ በቤተ መጻሕፍቱ መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በመዲናዋ በርካታ የመዝናኛ ቦታዎች ቢኖርም የህብረተሰቡን አዕምሮ ሊያበለጽጉና እና ሊያሳድጉ የሚችሉ ቦታዎች ውስን ናቸው ያሉት አቶ ደጀኔ፤ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ይህንን ችግር ሊቀርፍ የሚችል ነው ብለዋል።

ወጣት  ያብባል ባሳዝን በበኩሉ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሰረተ ልማት ያለው በመሆኑ፤ አካል ጉዳተኝነቱ  ሳይገድበው የቤተ መጻሕፍቱ ቋሚ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት አኮኖሚክስ ተማሪው ሂካ መርጋ፤ ቤተ መጻሕፍቱ ለሚማረው የትምህርት መስክ  የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚችልበትን ምቹ የማንበቢያ ቦታ እንደፈጠረለት ጠቁሟል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች አክለውም በቀጣይ ቤተ መጻሕፍቱ ለመማር ማስተማር የሚረዱ አዳዲስ መጻሕፍትን በፍጥነት እንዲያሟላም ጠይቀዋል።

አያይዘውም ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ብቻ የሆነውን የአገልግሎት መስጫ ጊዜውን ቢያራዝም መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ በተለያዩ ክልሎች አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር እንደ አብርሆት ያሉ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤተ መጻሕፍት  ሊስፋፉ ይገባል ብለዋል፡፡

የአብርሆት ቤተ መጻሕፍት ዳይሬክተር ኢንጅነር ውባየሁ ማሞ በበኩላቸው የአበርሆት ቤተ መጻሕፍት አንባቢ ትውልድን ለማፍራት ብሎም ለመማር ማስተማር አስፈላጊ መጻሕፍትን በአንድ ማዕከል ማግኘት እንዲቻል ታስቦ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል፡፡

ቤተ መጻሕፍት ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ በቀን  ከ5 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎችን  እያስተናገደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በቀጣይም ተጠቃሚዎች የሚያነሷቸውን የማንበቢያ ሰዓትን የማሻሻልን እና አዳዲስ መጻሕፍትን በየወቅቱ የማሟላት ጥያቄዎችን ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

አያይዘውም ቤተ መጻሕፍቱን ሙሉ በሙሉ ዲጅታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

 ቤተ መጻሕፍቱ አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ተቋማት፤ ግለሰቦችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጽሐፍ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነባው ቤተ መጻሕፍቱ ከ4 ሚሊዮን በላይ መጻሕፍትን የመያዝ አቅም አለው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም