ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች ጥራትን መሰረት አድርገው መስራት አለባቸው -ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

ጥቅምት 20 ቀን 2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች ጥራትን መሰረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።

9ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት በታላቁ ቤተመንግስት ተካሂዷል።

በመርሃግብሩ ላይ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ብቁ የሆኑ ከ40 በላይ የምርትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች የጥራት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በዚህ ወቅት፤ እንደ ሀገር ለማደግ፣ የህዝባችንን ኑሮ ለመለወጥና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራት ማዕከላዊ የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት ብለዋል።

በጥራት ብቁ ሆኖ ለመገኘት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተወዳዳሪዎች የተሻሉ ሆኖ መገኘትና የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዓለም እየተራቀቀችና በቴክኖሎጂ እያደገች ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ለዚህ በቁ ሆኖ መገኘት ተገቢ ነው ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በጥራት ዙሪያ የታዩ ለውጦች ቢኖሩም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ጥራት ገደብ የለውም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከሌሎች ሀገራት በጎ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለሀገራችን ማምጣትም የተቋሞቻችን ባህል ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና የህዝቡን ተጠቃሚነት የምናረጋግጥበት እንዲሆን ከመንግስት ባሻገር ሌሎች የልማት አጋሮችና ተቋማትም በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጥራት ስራ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ልማትና እድገት ለማፋጠን አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች ጥራትን መሰረት አድርገው መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና በበኩላቸው፤ ምርትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የመገምገሚያ መስፈርቶችን በመጠቀም በተደረገ ማጣራት አሸናፊ የሆኑትን መሸለማቸውን ተናግረዋል።

በዚህ መሰረት የተሸለሙ ምርትና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ተሞክሯቸውን ለሌሎች በማጋራት ሌሎች አምራችና አገልግሎት ሰጪዎች ለጥራት እንዲተጉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት ዘመኑ ጥራትን ብቻ መሰረት ያደረገ የንግድ ግብይት የሚደረግበት በመሆኑ ጥራት ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ድርጅት ተቋማትን ለማትጋት በየዓመቱ በዓለም አቀፍ መስፈርቶች ተመዝነው ብቁ የሆኑ አምራችና አገልግሎት ሰጪዎችን ይሸልማል ብለዋል።

የጥራት ሽልማት የተበረከተላቸው ድርጅቶች በበኩላቸው የጥራት ሽልማቱ በዓለም ገበያ ተወዳደሪ ሆኖ ለመውጣት የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ድርጅት ለለውጥና ራስን ለማዘመን መትጋት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አማካኝነት በ2000 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም