ቀጥታ፡

የሽብር ቡደኑ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰው የክህደት ሴራ በሰራዊቱና በህዝቡ የጠነከረ አንድነት ከሽፏል

ጋምቤላ ጥቅምት 20/2015 (ኢዜአ) 'የህወሓት የሽብር ቡደን በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም ሀገርን ለማፍረስ ያሰበው ሴራ በኢትዮጵያ ህዝብና በመከላከያ ሰራዊቱ የጠነከረ አንድነት ከሽፎ አገርን አስቀጥሏል ሲሉ በጋምቤላ የቀድሞ ስራዊት አባላት ገለጹ።

ጥቅምት 24'ን በማስታወስ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ የሰራዊት አባላት እንዳሉት የሽብር ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ክህደት በመፈጸም ሀገርን ለማፍረስ አስቦ የነበረው ሴራ፣ በመከላከያ ሰራዊቱ መስዋዕትነትና በኢትዮጵያ ህዝብ  መክሸፉን ነው።

ቀኑ  በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣ የክህደትና አረመኔያዊ ድርጊት በመሆኑም በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ መቼውንም የማይዘነጋ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑን አባላቱ ተናግረዋል።

ከሰራዊቱ አባላት መካከል ሃምሳ አለቃ ዘለቀ ደበሌ ለኢዜአ እንዳሉት የህወሓት የሽብር ቡደኑ "በአፈጣጠሩ ሰይጣን ይቅደመው እንጂ በገቢሩ ከሳይጣን በላይ የሆነ አረመኔያዊ ቡድን ነው" ይላሉ።

ለዚህም ዋነኛ ማሳያው ለ20 ዓመታት ሰላሙን በማስጠበቅ በልማቱም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ሲያግዘው የነበረውን የአብራኩን ልጅ የመከለከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝን ከጀርባው በመውጋት የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ነው ብለዋል።

የሽብር ቡዱኑ በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ክህደት ሀገርን ለማፍረስ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን በማጠናከርና እንደ ንብ በማበር የሽብር ቡድኑን ሴራው በጀግንነቱ ማክሸፉን ተናግረዋል።

የህወሓት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ መቼውንም የማይዘነጋ ጥቁር ታሪክ ነው ያሉት ደግሞ የቀድሞው የባህር ኃይል አባል የነበሩት ኡሞድ ሜት ናቸው።

ድንበር ከመጠበቅ ባለፈ በግብርና የልማት ስራዎች ጭምር ሲሳተፍ የነበረውን ሰራዊት የሽብር ቡድኑ ከጀርባው መውጋቱ የካሃዲነቱ ዋነኛ ማሳያነው ሲሉም ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያን ከሚጠሉ አንዳንድ ምዕራባዊያን ጋር በመታገዝ ሀገሪቱን ለማፍረስ እየሰራ ቢሆንም በጠነከረ ህዝባዊ አንድነትና በሰራዊቱ ጀግንነት እየተመከተና ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን   ተናግረዋል። 

የህወሓት የሽብር ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ መቼውንም የማይዘነጋ ጥቁር ሆኖ ይዘከራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም