ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ተቋማት ለሀገር ዕድገትና ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ ለመሆን ለጥራት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ ይገባል-ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ

ጥቅምት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ተቋማት ለሀገር ዕድገትና ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ ለመሆን ለምርትና አገልግሎት ጥራት ልዩ ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ።


9ኛው ሀገር አቀፍ የተቋማት የጥራት ሽልማት ዛሬ በታላቁ ቤተ-መንግስት የተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ብቁ የሆኑ ከ40 በላይ የምርትና አገልገሎት ሰጪ ድርጅቶችም የጥራት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ በዚህ ወቅት፤ እንደ ሀገር ለማደግ፣ የህዝባችንን ኑሮ ለመለወጥና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን ጥራት ማዕከላዊ የትኩረት አቅጣጫ መሆን አለበት ብለዋል።

በጥራት ብቁ ሆኖ ለመገኘት ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ማሟላት ቀዳሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከተወዳዳሪዎች የተሻሉ ሆኖ መገኘትና የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዓለም እየተራቀቀችና በቴክኖሎጂ እያደገች ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ለዚህ ብቁ ሆኖ መገኘት ተገቢ ነው ብለዋል።

ባለፉት አራት ዓመታት በኢትዮጵያ በጥራት ዙሪያ የታዩ ለውጦች ቢኖሩም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።

ጥራት ገደብ የለውም ያሉት ፕሬዚዳንቷ፤ ከሌሎች ሀገራት በጎ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ለሀገራችን ማምጣትም የተቋሞቻችን ባህል ሊሆን እንደሚገባ አንስተዋል።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውና የህዝቡን ተጠቃሚነት የምናረጋግጥበት እንዲሆን ከመንግስት ባሻገር ሌሎች የልማት አጋሮችና ተቋማትም በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ ሀገር ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት የጥራት ስራ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ለሀገሪቱ ምርትና አገልግሎት ጥራት መሻሻል በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት አማካኝነት በ2000 ዓ.ም ነው የተቋቋመው።

በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕቴዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና፣ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም