ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢ ወሳኝ ነው-የገቢዎች ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ገቢ ወሳኝ ነው-የገቢዎች ሚኒስቴር
ጥቅምት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ እድገት ዘላቂነት አስተማማኙ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገቢ ነው ሲሉ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ ዓይናለም ንጉሴ ገለጹ።
የተቋሙ የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ በተካሔደበት ወቅት ሚኒስትሯ እንደገለጹት በተለያዩ መንገዶች ከውጭ የሚገኙ ገቢዎች ቢኖሩም ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰብ ገቢ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል።
ሀገራችን ከምንም ጊዜ በላይ አሁን ገቢ የሚያስፈልጋት እንደመሆኑ ገቢን በሚፈለገው መጠን ለመሰብሰብ ሁሉም ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች የሰው ኃይላቸውን በትጋት በማንቀሳቀስ ሥራዎችን በልዩ ትኩረትና ርብርብ መሥራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በዓመቱ ከፍተኛ ገቢ ከሚሰበሰብባቸው ወራት መካከል የጥቅምት ወር አንዱ በመሆኑ የተያዘውን ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የመሰብሰብ ዕቅድ ለማሳካት አቅምን አሟጦ መጠቀም ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በገቢ አሰባሰብ ስራ ላይ የቴክኖሎጂ ችግር እንዳያጋጥም መስራት፤ ካጋጠመም በፍጥነት ለመፍታት እንዲቻል ቋሚ የድጋፍ ስልት መዘርጋት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በ2015 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከሀገር ውስጥ ታክስ ፣ከወጪ ንግድና ቀረጥ 95 ቢሊየን 184.36 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ93 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡንና ይሄም የዕቅዱ 98.07 በመቶ መሆኑ ተጠቅሷል።
የሩብ ዓመቱ አፈጻጸምም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ23 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ ያሳየ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ወደ 9 ቢሊዮን ብር የሚጠጋው ከውዝፍ እዳ የተሰበሰበ መሆኑም ተመልክቷል።
ቀሪ የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ከታቀደው በላይ ለማሳካት ግብር ከፋዮች እና ባለድርሻ አካላት ከተቋሙ ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።