የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ገበያን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ገበያን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገለጸ
ጥቅምት 19/2015/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ዓለምአቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ወደ ስራ እንዲገባ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እዮብ ገብረኢየሱስ ገለጹ።
መንግስት የካፒታል ገበያን ማቋቋም ማቀዱን ተከትሎ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገበያውን ማቋቋም የሚያስችለውን አዋጅ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ማጽደቁ ይታወሳል።
ገበያውን ወደ ተግባር ለማስገባትም የተቋማዊ አደረጃጀት፣ የህግ ማዕቀፎች፣ የሰው ሃይል ማብቃትና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑ መሆን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም ባንኩ ኤፍ.ኤስ.ዲ አፍሪካ ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ላለፉት ሁለት ዓመታት በዓለምአቀፍ አክሲዮን ገበያና ኢንቨስትመንት ዙሪያ ላሰለጠናቸው ባለሙያዎች የእውቅና መርሃ-ግብር አካሂዷል።
የብሄራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እዮብ ገብረኢየሱስ በዚሁ ወቅት፣ ዘርፉ እውቀትና ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች እንዲመራ ባንኩ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ለካፒታል ገበያው እውን መሆን የሚረዳ የአቅም ግንባታ ስልጠና ዘላቂ ለማድረግ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ትምህርት ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም በፋይናንስ ዘርፍ በቀጥታ የተሰማሩትንም ሆነ በተዛማጅ የሚመለከታቸውን ተዋንያን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በስኬት ስራ ላይ እንዲውል ብሔራዊ ባንክ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካፒታል ማርኬት ከፍተኛ አማካሪ አቶ አሰፋ ሱሞሮ በበኩላቸው፣ የካፒታል ገበያን እውን ለማድረግ እየተደረጉ ካሉ ጥረቶች መካከል ዓለም አቀፍ ስልጠና መስጠት ትኩረት የተሰጠው ነው ብለዋል።
በዚህም እስካሁን ከ500 ለሚበልጡ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።
የእንግሊዙ ቻርተርድ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኢንቨስትመንት ተወካይ ሚስዝ አቢ ኮርኒሽ ደግሞ፣ የተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ በሚገባ እስኪስፋፋ ድረስ ከብሔራዊ ባንክና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት ጋር በመተባበር የሚደረገው ድጋፍ ይቀጥላል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የንግድ ስራ ትምህርት ቤት ዲን ተወካይ ዶክተር ሙሉጌታ ገብረመድህን በበኩላቸው፣ የንግድ ስራ ትምህርት ቤቱ ለዚህ ዓለም አቀፍ ስልጠና አጋርነቱን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል።
ስልጠናውን ከተከታተሉት መካከል የባንክ፣ የኢንቨስትመንትና ሌሎችም የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች፣ ኦዲተሮችና የህግ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ስልጠናው በቀጣይ ዙር ከየካቲት ወር ጀምሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
የካፒታል ገበያን በኢትዮጵያ ማቋቋም ያስፈለገው ካፒታል በማሰባሰብ፣ የገበያ ስርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች ለመደገፍና ስጋቶችን በመጋራት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ በማለም ነው።
ሌላኛው ግብ ኢንቨስተሮችን ለመጠበቅና ገበያውን ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ቀልጣፋ እንዲሆን እንዲሁም ከህዝብ ካፒታል መሰብሰብ የሚፈልጉ ሙዓለ ንዋየ አውጭዎች ከህዝብ ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስችላል።