ቀጥታ፡

ትዊተር የዘጋቸውና የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ አካውንቶች እንዲከፈቱ የማድረግ አላማ ያለው እንቅስቃሴ ተጀመረ

ጥቅምት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) ትዊተር የዘጋቸውን የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ ገጾችና የግለሰብ አካውንቶች ዳግም እንዲከፈቱ የማድረግ ዓላማ ያለው እንቅስቃሴ ተጀምሯል።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ “ምንም ጥፋት ሳያጠፉ እውነትን ብቻ በመናገራቸው ብቻ የታገዱ የትዊተር አካውንቶች ዳግም መከፈት አለባቸው” ብላለች።

ትዊተር ኢትዮጵያን ደግፈው የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የማኅበረሰብ አንቂዎችን ገጽ መዝጋቱ ይታወቃል።

‘የዲፌንድ ኢትዮጵያ ታስክ ፎርስ ኢሮፕ’፣ ‘ኖሞር ሃብ’ ፣ትውልደ-ኢትዮጵያዊው ነቢዩ አስፋው፣ትውልደ-ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊት ዶክተር ሚድል ላንደርና ሌሎችም ገጾች ከተዘጉት ገጾች መካከል ይገኙበታል።

እርምጃው የኢትዮጵያን ድምጽ ለማፈንና ለመገደብ የተደረገ መሆኑንም በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እየገለጹ ይገኛሉ።

ይሄንንም በመቃወም በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተደጋጋሚ ጊዜ በኩባንያው መቀመጫ ሳን ፍራንሲስኮ ከተማ በሚገኘው የትዊተር ዋና መስሪያ ቤት ሰላማዊ ሰልፎችን ሲያካሄዱ ነበር።

ትናንት የዓለም ቁጥር አንድ ባለሀብት ኤለን መስክ ቲዊተርን በ44 ቢሊዮን ዶላር መግዛቱ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።

በ”ነጻ ሃሳብ” እንደሚያምን የሚነገርለት ኤለን መስክ ትዊተርን መግዛቱን ተከትሎ ኩባንያው የዘጋቸውን የኢትዮጵያን እውነት የሚያስረዱ ገጾችና የግለሰብ ‘አካውንቶች’ ዳግም ማስከፈትን አላማ ያደረገው የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ መጀመሩን ኢዜአ ከአስተባባሪዎቹ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ “ምንም ጥፋት ሳያጠፉ እውነትን ብቻ በመናገራቸው የታገዱ የትዊተር አካውንቶች ዳግም መከፈት” አለባቸው ስትል ቀደም ሲል ተቋሞዋን ገልጻለች።

በዘመቻው “ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት መከበር አለበት”፣”ነጻ ሃሳብ የዴሞክራሲ መሰረት ነው” ፤ ”የኢትዮጵያ ድምጾች መታፈንና መገደብ የለባቸውም” ፣ ”ትዊተር የዘጋቸውን የኢትዮጵያ ደጋፊ ገጾች መልሶ ይክፈትና “ኤለን መስክ የታገዱት የትዊተር ገጾች እንዲከፈቱ ያደርጉ” የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ይገኛሉ።

ትዊተር የዘጋውን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃዎች የሚንሸራሸሩባቸውን ገጾች (ትሬንድስ) በድጋሚ መክፈት ይኖርበታልም ብለዋል አስተባባሪዎቹ።

በ”ነጻ ሃሳብ” የሚያምነው ኤሎን መስክ ትዊተርን መግዛቱ ገጾቹን ድጋሚ ወደ አገልግሎት ለመመለስ መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን፣ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተጀመረውን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ እንዲቀላቀሉም ጥሪ ቀርቧል።

የዓለም ቁጥር አንድ ባለሃብት ኤለን መስክ በሰጠው አስተያየት “ነጻ ንግግር የዲሞክራሲ መሰረት ነው፤ ትዊተር ደግሞ ለሰው ልጅ ቀጣይ ሕይወት ወሳኝ ጉዳዮች የሚከራከሩበት የዲጂታል ከተማ አደባባይ ነው" ብሏል።

የኩባንያው አርማ የሆነችው “ድንቢጥ ወፍ ነጻ ወጣች” ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም