ቀጥታ፡

የአፍሪካ የወደፊት ትልቁ ተስፋዋ በአንድነቷና በነገ መሪ ወጣቶቿ ላይ የተመሰረተ ነው

ጥቅምት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአፍሪካ የወደፊት ትልቁ ተስፋዋ በአንድነቷና በነገ መሪ ወጣቶቿ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተገለጸ።

እኤአ የ1950ዎቹና 60ዎቹ አፍሪካውያን ወጣቶችና መሪዎች ትግል በቀኝ ግዛት ስር የወደቁ ሀገራትን በተባበረ ክንድ ነጻ የማውጣትና የወደፊቷን አፍሪካ መቅረፅ ላይ ያተኮረ ነው።

የፓን አፍሪካኒዝም ታጋይ ክዋሜ ንክሩማህ፤ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት በይፋ የተላቀቀች ቢሆንም ከእጅ አዙር አገዛዝ ግን አሁንም አልተላቀቀችም ብለው ነበር።

በቅኝ ግዛት ዘመን ሀብቷን የመዘበሩ፣ ትውልዷን የጨፈጨፉ፣ ባህሏን ያራቆቱ፣ የነገ ተስፋዋን የነጠቁ ኃይሎች አፍሪካውያንን ለመከፋፈልና ዳግም በባርነት ለመበዝበዝ እያሴሩ መሆኑንም እንዲሁ።

ይህን ለማክሸፍ ምልዑ ነጻነትን ማረጋገጥ፣ ድክመትን መለየት፣ አንድነትን ማጠናከርና የአፍሪካን ማህበረ ኢኮኖሚ ማሻሻል እንደሚገባ በመጠቆም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በ35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ “አፍሪካውያን አንድ ከሆንን እንነሳለን፤ ከተከፋፈልን ግን እንወድቃለን” ማለታቸው አይዘነጋም።

አፍሪካ ካላት ህዝብ መካከል አብዛኛው ወጣት መሆኑ አህጉሪቱን አንድነቷን በማጽናት ከድህነት አረንቋ ለማላቀቅና ብልጽግናዋን ለማሳካት ትልቅ አቅም በመሆኑ ይህንን ወደ ተግባር ለመለወጥ ጊዜው አሁን ነው ብለውም ነበር።

የሰላምና ግጭት ተመራማሪና ተንታኝ ድጋፌ ደባልቄ የ20ኛው ክፍለ ዘመን የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የሰንደቅ ዓላማ ነጻነትን ብቻ እንዳቀዳጀ ጠቅሰው ነጻነት ምልዑ የሚሆነው በኢኮኖሚውም ሲደገም ነው ይላሉ።

የአፍሪካ የወደፊት ትልቁ ተስፋዋ አንድነቷና ወጣቶቿ ናቸው ያሉት ተመራማሪው፤ የቀደምት አፍሪካውያን መሪዎችን ህልም ለማሳካት ወጣቶች  የአፍሪካን ብሩህ ዘመን በተባበረ ጥረታቸው እውን ሊያደርጉት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ኬንያዊው ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ለአዲስ ተሿሚ የኢትዮጵያ ሚኒስትሮች፤ ባደረጉት ገለፃ አፍሪካ ማንም የተመጽዋጭነት ጥሪ የሚያቀርብላት፣ መሪዎቿም በኩራት ምፅዋት የሚቀበሉበት ዘመን እንዲያበቃ መስራት ለነገ የማይባል ስራ ነው ብለዋል።

ከየትውኛውም ሀገር የሚመጣ እርዳታና ብድር አህጉሪቱ ከተዘፈቀችበት ችግር የሚያላቅቃት አለመሆኑን አብራርተው ይህን ለመቀየር የዘመኑ ፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ የኢኮኖሚ አርነትን ማካተት አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

“የአፍሪካ የኢኮኖሚ ፓወር ሀውስ”  የመሆን አቅም ያላት ኢትዮጵያ መሪዎችና ህዝቧ አድካሚውንና በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሳካውን የዘመኑን የፓን አፍሪካኒዝም ጉዞ ለማሳካት ከፊት እንዲሰለፉም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም