የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ለማጠናከር የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ሚና ከፍተኛ ነው--አቶ መላኩ አለበል

159

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥቅምት 19 ቀን 2015 "የግብርና ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በማገዝ በኩል የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ሚና የጎላ ነው" ሲሉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ገለጹ ።

የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ መድረክ የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና ባለሀብቶች በተገኙበት በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ እሴት የተጨመረባቸው የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

እንደ ሀገር ወደ ስራ እየገቡና በሥራ ላይ ለሚገኙ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች መንግስት በከፍተኛ በጀት መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢኮኖሚ ዘርፍም የሚታሰበውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ አስተዋጾው የጎላ በመሆኑ ዘርፉን የማጠናከርና ተወዳዳሪነቱን የማሳደግ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ መላኩ ጠቁመዋል።

ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ለአብነት እንደሚጠቀስ ገልጸው፣ "ፓርኩ በአካባቢው ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያበረክተውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበት መሆኑንም ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ባለሀብቶች በፓርኩ እንዲሰማሩ የጠየቁት ሚኒስትሩ፣ "በዘርፉ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መንግስት በቂ ድጋፍ ያደርጋል" ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው ክልሉ ለፓርኩ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችል እምቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል።

"በፓርኩ ውስጥ የመስራት ፍላጎት ያላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በቂ ድጋፍ ይደረጋል" ሲሉም ገልጸዋል።

የይርጋለም የተቀናጀ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም