ቀጥታ፡

ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበት የታደሰው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለምረቃ በቃ

ጥቅምት 19/2015( ኢዜአ)  ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ።

የቴአትር ቤቱ እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ በዛሬው ዕለት በይፋ የምርቃት ሥነሥርዓቱ ተከናውኗል።

ለሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መቋቋም ምክንያቱ በሐምሌ 11 ቀን 1927 ዓ.ም የፋሽስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል መስፋፋት ያሳሰባቸው ወጣቶች እንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ከሀገራቸው ተሰደው ፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩት መኮንን ሀብተወልድ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ግንቦት 4 ቀን 1935 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ማኅበር የሚለውን ስያሜ ማውጣታቸው ይታወሳል።

የሀገር ፍቅር ቲአትር ቤት በ1948 ዓ.ም ተገንብቶ አሁን ያለውን ቅርፅ ለመያዝ መብቃቱም ተገልጿል።

ባለፉት 20 ዓመታት ምንም ዓይነት ዕድሳትና ማሻሻያ ሳይደረግለት ቆይቷል።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበባት ቱሪዝም ቢሮ በ2013 ዓ.ም የእድሳት ሥራ አስጀምሮ አሁን ላይ በመጠናቀቁ ለምርቃት በቅቷል።

በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበባት ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሣው፤ ለዕድሳቱ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ተናግረዋል።

የቴአትር ቤቱ እድሳትም ደረጃውን ጠብቆ በጥሩ ሁኔታ በመጠናቀቁ ለአገልግሎት መብቃቱን አብስረዋል።

ለዕድሳቱ ከፍተኛ ድርሻ ለነበራቸው ሁሉ በማመስገን በኪነ ጥበብ ዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በቢሮው የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሠርፀ ፍሬስብሐት፤ ከሀገር ህልውና ጋር ተያይዞ ከረጅም ዓመታት በፊት የተመሰረተው የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በመታደሱ ሁላችንንም አስደስቷል ብለዋል።

ከኢጣሊያ ወረራ በኋላም ጠላት የሸረሸረውን የሀገሪቱን ባህልና የሞራል መሠረቶች ለማቃናትና ለማነፅም ቴአትር ቤቱ ቀዳሚ እንደነበር ገልፀዋል።

ለዚህም በኢጣሊያ ወረራ ወቅት ሀገር መነካቱ እንደማይቀር ያሳሰባቸው ወጣቶች ቴአትር ቤቱን መመስረታቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዕድሳቱም "አዲስ ባይሰራ ያለውን አድሶ ለትውልድ ማሻገር ያስፈልጋል" በሚል ዓላማ ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ የእድሳት ስራው ተከናውኗል ብለዋል።

የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዳይሬክተር አብዱልከሪም ጀማል፤ቴአትር ቤቱ በኪነጥበቡ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን ያከናወነ ታሪካዊ ተቋም መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የቴአትር ቤቱ እድሳት መጠናቀቁን ተከትሎ መደበኛ ትርኢቱን ከመስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ማቅረብ መጀመሩን አስታውሰዋል።

የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከሰሃራ በታች አገራት የመጀመሪያው ቴአትር ቤት መሆኑን የታሪክ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም