ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት የፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር ወሳኝ ነው--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

181

ጥቅምት 19 ቀን 2015 (ኢዜአ) አፍሪካ አሁን እየገጠሟት ላሉት ፈተናዎች እልባት ለመስጠት የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የአፍሪካ ወጣቶች የወደፊት የአህጉሪቷን እጣ ፈንታ የመቅረጽ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

አፍሪካ በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የጸጥታን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት በትብብር መስራት እንደሚገባና ለዚህም የፓን አፍሪካኒዝም መጠናከር ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

የአፍሪካ 70 በመቶ ሕዝብ ወጣት ነው ያሉት አቶ ደመቀ ወጣቱን ያሳተፈ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በኢነርጂና በብሔራዊ አንድነት ላይ ስትራቴጂካዊ የሆነ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት በአጀንዳ 2063 እና በሌሎች የፖሊሲ ማዕቀፎቹ ላይ በወጣቶች ልማት ላይ እየሰራ ያለው ተግባር የሚደነቅ ነው ብለዋል አቶ ደመቀ።

ኢትዮጵያ በብሔራዊ የወጣት ፖሊሲዋ ወጣቶች በአገር ግንባታ፣ በሰላም፣ በአመራርነትና በውሳኔ ሰጪነት ላይ ተሳትፎ እንዲኖራቸው እየሰራች እንደምትገኝም አመልክተዋል።

ሃገራችን ብሔራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደምትገኝና በመርሐ-ግብሩም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶች እየተሳተፉበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ወጣቶች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው አውስተዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች የአፍሪካ መጻኢ እድልና እድገት የመወሰን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ይሄንንም ያሳኩታል ብዬ አምናለሁ ነው ያሉት አቶ ደመቀ በንግግራቸው።

የአፍሪካ ወጣት ትውልድ ፓን አፍሪካኒዝምን የአፍሪካን ራዕዮች ለማሳካት ሊጠቀምበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት የአፍሪካ ወጣት መሪዎች ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ይቆያል።

የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስተዋወቅና አብሮነትን ማጠናከር ዓላማው ባደረገውና በዚህ ጉባዔ ከ50 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣት መሪዎችና የአፍሪካ አገራት የቀድሞ መሪዎች ይሳተፋሉ።

በጉባኤው የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉም ይጠበቃል።

በአፍሪካ ትብብርና ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የምርምርና ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ለማወቅ ተችሏል።

ከወጣቶቹ በተጨማሪ በሕይወት የሌሉ የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ታጋዮች ቤተሰቦች በጉባኤው ላይ የሚታደሙ ሲሆን፤ ለታጋዮቹ ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም