ቀጥታ፡

በመላው ዓለም የሚገኙ 17 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጥምረት አባላት በውይይቱ ውጤት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ተግባር ተቃወሙ

ጥቅምት 19/2015/ኢዜአ/ በመላው ዓለም የሚገኙ 17 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ጥምረት አባላት በውይይቱ ውጤት ላይ ያልተገባ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላትን ተግባር ተቃወሙ፡፡

የጥምረቱ አባላት ባወጡት መግለጫ መንግስት በትግራይ እያካሄደ ያለውን ተግባር እንደሚደግፉ ገልጸው፣ ህጋዊ የሆነው የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ያለውን ውይይት ጨምሮ እያከናወናቸው ባሉ ተግባራት ላይ አንዳንድ ሀገራት የሚፈጥሩትን ያልተገባ ጫና እንቃወማለን ብለዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ግጭትና ውድመት ህወሀት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መምጣቱን አስታውሰው፣ መንግስት ለሰላም ካለው ጽኑ ፍላጎት በመነሳት ከፍተኛ ውድመት ያስከተለውን ይህን ግጭት ከቀሰቀሰው አካል ጋር ያለቅድመ ሁኔታ በመነጋገር ሰላማዊ መፍትሔ ለማምጣት ፍላጎቱን በተደጋጋሚ አሳይቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያም ሆነ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን የውይይት ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በውይይቱ ላይ በመሳተፍ ላይ ላለው የኢትዮጵያ መንግስትና ውይይቱን ላመቻቹ አካላት አባላቱ ድጋፋቸውን ገልጸው፣ ውይይቱን ተገን አድርጎ በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና በመፍጠር በመስዋዕትነት የተገኘውን ድል ለመንጠቅ የሚደረገውን እቅስቃሴ እንቃወማለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በውይይቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ ጠቅሰው፣ አሸባሪ ቡድኑ እንደገና እንዲደራጅና ለሌላ ጥፋት ዕድል እንዲያገኝ የሚያደርጉ ማናቸውንም ምክረ ሀሳቦች እንደማይደግፉ ገልጸዋል።

አንዳንድ ሀገራትና አለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎችም አካላት ጥቅማቸውን ለማስከበርም ሆነ የተፈጠሩ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ በማጣጣር ላይ ያለውን ህወሀትን ትተው የኢትዮጵያ መንግስትን ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የውይይቱን ውጤት ለመቀየር የሚደረጉ ማናቸውንም አይነት ጫናዎች እንደሚቃወሙ ገልጸው፣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ከግጭት ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት በሚችሉት ሁሉ ለመደገፍ ሁልጊዜም ዝግጁ ነን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም