ቀጥታ፡

አየር መንገዱ ለተጓዞች የሚያቀርበውን ምግብና መጠጥ በሚፈለገው ልክ ከአገር ውስጥ መተካት አልቻለም

አዲስ አበባ  መስከረም 15/2011 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተጓዦች ለሚያቀርበው ምግብና መጠጥ 80 በመቶ ከአገር ውስጥ አምራቾች ለመቀበል ቢያቅድም በሁለት ዓመት ውስጥ 30 በመቶውን ብቻ እየተቀበለ እንደሆነ ተገለጸ። አየር መንገዱ  በቀን ከ45 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተጓዦቹ የሚያቀርበው ምግብና መጠጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከውጭ በሚገባ የምግብ ግብዓት ነው ብሏል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አሰፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳሉት ለተጓዦች የሚቀርብ ምግብና መጠጥ ከአገር ውስጥ አምራቾች 80 በመቶ ያክሉ እንዲቀርብ እየተሰራ ነው። ይሁን እንጂ ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ጋር ለመስራት ከሁለት ዓመት በፊት ጅምሮች ቢኖሩም እስካሁን 30 በመቶ ያክል አቅራቢዎች ብቻ ናቸው ምርታቸውን ለአየር መንገዱ የሚያቀርቡት ብለዋል፤ ይህም ደግሞ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘሮች ብቻ መሆናቸውን በማውሳት። በመሆኑም ከአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው ጥረት በቂ ባለመሆኑ የተሻለ ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል። በአሁኑ ወቅት ከ50 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ቢኖሩም አየር መንገዱ ከሚፈልገው አንጻር ዝቅተኛ መሆኑ ነው የሚናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው። በተጨማሪም ለምግብ አቅርቦቱ 300 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ አብራርተዋል። አቅርቦቱን በአገር ውስጥ ምርት መተካት አለመቻልም አገሪቷን ለአላስፈላጊ የውጭ ምንዛሪ እየዳረጋት እንደሆነም አብራርተዋል። በዚህም የአገር ውስጥ አምራቾች ምርታቸውን ለአየር መንገዱ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑና አገሪቱ ለውጭ ምርት የምታወጣን ወጪ አገር ውስጥ ማስቀረት እንዲቻል በጋራ ለመስራት የሚያስችል ጥሪ አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር የገበያ ትስስር ለመፍጠርም የጎላ ሚና እንዳለው በመጠቆም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም