በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ምርታማነታቸው እያደገ መምጣቱን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ
ዲላ (ኢዜአ) ጥቅምት 18/2015 የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን መጠቀም በመጀመራቸው ምርትና ምርታማነታቸው ከእጥፍ በላይ እያደገ መምጣቱን በጌዴኦ ዞን የዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።
የደቡብ ክልልና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ አመራሮች በወረዳው በኩታ ገጠም የለማ የቡና ማሳ የመስክ ምልከታ አድርገዋል።
በወረዳው የጎላ ቀበሌ አርሶ አደር ዳንኤል ሾጦጦ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከሁለት ዓመት በፊት በ4 ሄክታር ማሳቸው ላይ የነበረን ያረጀ ቡና ነቅለው በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች መተካታቸውን ጠቅሰዋል።
የተሻሻሉት ዝርያዎች በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ምርት መስጠት ከመጀመራቸው ባለፈ ከነባሩ ዝርያ አንጻር የሚሰጡት ምርት ከሁለት እጥፍ በላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ነባሩ የቡና ዝርያ ጥሩ ምርት በያዘ ዓመት በሄክታር ከአምስት ኩንታል በላይ አይሰጥም ያሉት አርሶ አደሩ፣ ከተሻሻሉ ዝርያዎች ከአንድ ሄክታር ከ17 ኩንታል በላይ እሸት ቡና መሰብሰባቸውን ጠቁመዋል።
የተሻሻለው ዝርያ ከምርታማነቱ በላይ ጥራትና መጠኑም የተለየ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን በኩታ ገጠም ማልማት የተሻለ ምርት እንደሚሰጥ ማረጋገጣቸውን የጠቀሱት ደግሞ አርሶ አደር ወርቁ ወሬራ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በኩታ ገጠም ካለሙት ሦስት ሄክታር የቡና ማሳ በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ ምርት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም ከነባሩ ምርት አንጻር ሲታይ ከእጥፍ በላይ መሆኑን ነው አርሶ አደሩ ያስረዱት።
በተያዘው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ምርት የአቅራቢነት ፍቃድ በማውጣት ቡናቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
በወረዳው ከ500 ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ የነበሩ ያረጁ ቡናዎችን በመንቀል በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች በመተካት በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተገኝ ታደሰ ናቸው።
"ይህም የወረዳውን ዝቅተኛ የቡና ምርታማነት ከማሻሻል ባለፈ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው" ብለዋል።
በወረዳው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በተያዘው የምርት ዘመን ከ10ሺህ 651 ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የጌዴኦ ዞን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ከተሰራ ለውጥ እንደሚመጣ የዲላ ዙሪያ ወረዳ አርሶ አደሮች ጥሩ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይ ያረጁ ቡናዎችን ነቅሎ በተሻሻሉ ዝሪያዎች በመተካት ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወረዳውን ተወዳዳሪ ቡና አምራች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ሃላፊው እንዳሉት በጥቂት አርሶ አደሮች የታየውን ምርጥ ተሞክሮ በቀጣይ ወደ ሁሉም የዞኑ አርሶ አደሮች በማስፋት የተገኝውን ውጤት ማጠናከር ይገባል።
የደቡብ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዲስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሃልገዮ ጂሎ በበኩላቸው በወረዳው ቡናን በኩታ ገጠም በማልማት የተገኝው ውጤት የሚበረታታ ነው ብለዋል።
በተለይ የተሻሻሉ ዝሪያዎችንና የግብርና ቴክኖሎጅ ተጠቅሞ ቡናን ከሌሎች ሰብሎች ጋር በስብጥር በማልማት ምርታማነትን ማሳደግና በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባም አስረድተዋል።
በዚህ ረገድ በወረዳው የታየው መልካም ጅምር መጠናከርና መስፋት እንዳለበት ነው ያስገነዘቡት
በጌዴኦ ዞን በተያዘው የምርት ዘመን 100ሺህ ቶን ቡና በመሰብሰብ ከ29ሺህ ቶን በላይ የሚሆነውን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።