ቀጥታ፡

በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን የ”ስማርት ሲቲ” አሠራርን ስራ ላይ ማዋል ይገባል-ሚኒስቴሩ

አርባ ምንጭ ጥቅምት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ).በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የ”ስማርት ሲቲ” አሠራርን ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በ”ስማርት ሲቲ” ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የከተሞች ፎረም በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በፎረሙ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፈንታ ደጀን እንደገለጹት ከተሞች የአስተዳደር፣ የገበያና የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት በመሆናቸው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ለውጥ ዕድገት ምሶሶዎች ናቸው።

ከተሞች የህዝብ ቁጥር መጨመርን  በአግባቡ ከተጠቀሙት ሀብት ካልተጠቀሙት ደግሞ ስጋት ነው" ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው በሀገሪቱ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ከ1 ሺህ በታች የነበሩ ከተሞች አሁን ላይ 2ሺ 500 መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

"በከተሞች ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርአት አለመዘርጋቱ፣ በፕላን እንዲመሩ ምቹ ሁኔታዎች አለመፈጠራቸውና  በከተሞች ዕድገት ዙሪያ ወጥ ግንዛቤ አለመኖር በዜጎች ላይ የመልካም አስተዳር ችግር እየፈጠረ ይገኛል "ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከተሞች በፕላን እንዲመሩና ዜጎች ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኙ የ”ስማርት ሲቲ” አሠራርን መተግበር አስፈላጊ መሆኑን አስታውቀዋል።

 “ስማርት ሲቲ”  ከተሞች ማራኪና ሳቢ ለሰው ልጆች ምቹ የሚሆኑበት የአሠራር ስርአት መሆኑን ያስረዱት ደግሞ የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ አንዷለም ጤናው ናቸው።

የኢትዮጵያ ከተሞች የትብብር መድረክ በአሁኑ ሰዓት 72 ከተሞችን በአባልነት በማቀፍ ከተሜነትን በማስፋፋት የነዋሪዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የተለያዩ የከተማ ከንቲባዎች በከተማ አስተዳደርና ከተሜነት ሥርአት ዙሪያ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ልምድ እንዲቀስሙ ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ አገሪቱ ከያዘቻቸው ዘላቂ የልማት ግቦች አንጻር ከተሞች ለዜጎች ምቹ እንዲሆኑና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ ማርቆስ ማቴዎስ በበኩላቸው ከተማዋ ለበርካታ ዓመታት ያላትን ፀጋ መጠቀም ሳትችል መቆየቷን ጠቅሰው  "ከለውጡ ወዲህ የለውጡ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ጀምራለች" ብለዋል።

ከተማዋ ለቱሪስት መዳረሻ የሚሆኑ የአባያና ጫሞ ሓይቆች፣ የእግዜር ድልድይ፣ የአዞ ገበያ፣ የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም በአፍሪካ ብቸኛው የአዞ ርባታ መገኛ በመሆኗ  ለከተማዋ ትልቅ ፀጋ መሆኑን አውሰተዋል።

በከተማዋ በቅርቡ በተዘጋጀው ማስተር ፕላን መሰረት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት በአፍሪካ ከሚገኙ ቀዳሚ ከተሞች አንዷ እንድትሆን እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር፣ በከተሞች ትብብርና በከተሞች ገቢ ሪፎርም ትብብር  ለሁለት ቀን በተዘጋጀው ሀገር አቀፍ መድረክ ስለ “ስማርት ሲቲ” ጽንሰ ሀሳብ እና የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድገት ሁኔታን የሚገልጹ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

በመድረኩ ላይ ከአዘጋጅ ተቋማት በተጨማሪ የ40 ከተሞች ከንቲባዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም