የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች መቆጣጠር የሚችልበት አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል- የአገር ውስጥ ባንኮች የስራ ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች መቆጣጠር የሚችልበት አሰራር መዘርጋት ይኖርበታል- የአገር ውስጥ ባንኮች የስራ ኃላፊዎች
ጥቅምት 18 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የባንክ ስርእት ሲገቡ ህጋዊ አስራራቸውን የሚከታተልበትና የሚቆጣጠርበት ሂደት ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚገባው የአገር ውስጥ ባንኮች የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት "የውጪ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲሰሩ መፈቀዱ ያለው እድልና ተግዳሮት" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ከባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ ንግድና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
የዳሸን ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ ኢትዮጵያ የውጪ ሀገር ባንኮች እንዲገቡ መፍቀዷ ከሌሎች አገራት ተሞክሮ ሲታይ ወደ ኋላ ዘግይቷል ብለዋል።
ሆኖም ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻር የውጪ ባንኮች ስራ ከመጀመራቸው በፊት በቂ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል።
የውጪ ባንኮች ስራ ሲጀምሩም የብድር አሰጣጥን ለማቀላጠፍ፣ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንዲሁም ለቴክኖሎጂ ሽግግር በር ከፋች መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በቀጣይም የኢትዮጵያ ባንኮች በቅንጅት ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ምቹ ሁኔታዎች መፍጥር ይገባል ነው ያሉት አቶ አስፋው።
የሕብረት ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ መላኩ ከበደ በበኩላቸው የውጭ አገር ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ለመቆጣጠር እና ለመከታተል በሚያስችል መልኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ራሱን ማዘጋጀትና ለዚህም የሚሆን አሰራር ማበጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በአማራ ባንክ የገበያና የኢኮኖሚ ጥናት ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ወልዴ በበኩላቸው የውጪ ባንኮች መዋዕለ ነዋያቸውን ማፍሰስ ሲጀምሩ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የማሳደግ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ የውጪ ሀገር ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ መፈቀዱ የንግዱ ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።
ከዚህም ባለፈ ሕብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት እንዲያገኝና አገልግሎቶችንም በዘመነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።
"የኢትዮጵያ ባንኮች ከእርስ በእርስ ውድድር ይልቅ ፉክክራቸውን ከውጭ ባንኮች ጋር ማድረግ የሚያስችላቸውን አቅም መፍጠር አለባቸው" ብለዋል።
ለዚህም የቴክኖሎጂ፣የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅም ማጠናከር ይገባቸዋል ነው ያሉት ወይዘሮ መሰንበት።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሚያደርግ ረቂቅ ፖሊሲ በስራ ላይ እንዲውል መወሰኑ የሚታወስ ነው።