የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት የአይነት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት የአይነት ድጋፍ አደረገ
ጥቅምት 18/2015/ኢዜአ/ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡
በተመሳሳይ የአትሌት ድንቅነህ ሶዳ ፋውንዴሽን ለሰራዊቱ የአንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉን በመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ዳይሬክተር የሆኑት ብርጋዴር ጀነራል ዘላለም ፈተና ተረክበዋል።
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሃርቢ ቡህ በዚሁ ጊዜ የከተማ አስተዳደሩ ከኀብረተሰቡ ጋር በመተባበር ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡
በዛሬው እለትም ለአራተኛ ዙር የቁም እንስሳቶችን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ የከተማ አስተዳደሩ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ እስካሁን ባለው ሂደት ለሰራዊቱ በአራት ዙሮች በአጠቃላይ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ የአትሌት ድንቅነህ ሶዳ ፋውንዴሽን ለሰራዊቱ የአንድ መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
የፋውንዴሽኑ መስራችና ባለቤት አትሌት ድንቅነህ ሶዳ፤ አገር ተረካቢ ህጻናት ህልማቸውን የሚያሳኩት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ነጻነት ሲረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የአገር ሉአላዊነትን ለማስከበር መስዋዕትነት እየከፈለ የሚገኘውን የመከላከያ ሰራዊት መደገፍና ማበረታታት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጀነራል ዘላለም ፈተና በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ለሰራዊቱ እያደረጉት ያለው ድጋፍ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ ብርታት እንደሆነው ተናግረዋል፡፡
በዚህም ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።