ህብረተሰቡ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመንከባከብና በአግባቡ በመጠቀም ከድህነት መውጣት እንዲችል ማድረግ ይገባል - ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ

147

ሚዛን አማን፤ ጥቅምት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመንከባከብ በአግባቡ ተጠቅሞ ከድህነት መውጣት እንዲችል ማድረግ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤልያስ አስገነዘቡ።

ብሄራዊ  የሰውና ባዮስፌር ኮሚቴ ዓመታዊ ጉባኤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሚዛን-አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

በጉባኤው ላይ በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ እና የብሔራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፈሰር ኢያሱ ኤልያስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ አልምታ መጠቀም ከቻለች ለልመና እጇን አትዘረጋም።

በተለይ የአየር ጸባይ ተጽዕኖን መቋቋም የሚችል አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ላይ እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ዜጎች የተፈጥሮ ሀብቶችን እየጠበቁና እየተንከባከቡ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ከድህነት መላቀቂያ እንዲያደርጉ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ደን ሲጠበቅ ብዝሃ ህይወት እንደሚጠበቅ የገለጹት ፕሮፈሰሩ ለተግባሩ ውጤታማነት ህብረተሰቡን በማሳተፍ መስራት ተገቢ መሆኑን አክለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መልካም የሚባሉ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናቀቀው 2014 በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ነባር የተፋሰስ ልማቶችን በማደስ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ከእንስሳት እና ሰው ንኪኪ የጸዳ እንዲሆን መደረጉን አመላክተዋል።

የተፈጥሮ ልማትና ጥበቃ ሥራ የአፈር መሸርሸርን አስቀርቶ ለአርሶ አደሩ ለም መሬት በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን ማሳደጉን ተናግረዋል።

"እንደሀገር ያለንን ወንዝና አፈር በአግባቡ ከተጠቀምን ከበቂ በላይ ምርት ማምረት ይቻላል" ያሉት ፕሮፈሰር ኢያሱ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሥራን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና በኢኮኖሚ ጠንክራ ለመውጣት የነደፈችው ብሄራዊ የስንዴ ልማት ስትራቴጂ ትግበራ ረገድም ባለፈው ዓመት 107 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በራሷ አቅም ማምረቷን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በዓመት የሚያስፈልጋት 97 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መሆኑን ጠቁመው  ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ የሚሸፈነው 35 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ እንደነበር ገልጸዋል።

"አሁን ላይ ኢትዮጵያ ልማቱን በስፋት ማካሄድ በመቻሏ ለውጭ ገበያ የምታወጣውን ከ1 ቢሊዮን ዶላር  በላይ ታድናለች" ብለዋል።

"ህዝቡ ጠብቆት ያቆየውን የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ኢኮኖሚ እንዲያመነጭ እየተደረገ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብዝሀ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር  ዶክተር መለሰ ማሪዮ ናቸው።

ደኖች ሲጠበቁ፣ እንስሳትና እጽዋት እንዲሁም ወንዞች ስለሚበራከቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ 12 ነጥብ 3 በመቶ ያህል ጥብቅ አካባቢ እንዳለ ጠቅሰው በ2030 ዓም 30 በመቶ ያህል ጥብቅ የብዝሃ ህይዎት ማዕከል እንዲኖር ለማድረግ ታልሞ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው ብሄራዊ የሰውና የባዮስፌር ጉባኤ በፌዴራል ደረጃ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትና የዩኒቨርስቲ የዘርፉ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም