ቀጥታ፡

ኮሌጁ ለኢንዱስትሪው የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት የጀመረውን ሥራ ሊያጠናክር ይገባል---አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥቅምት 18/2015 የጋምቤላ ኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

የኮሌጁን የስልጠና አቅም ለማጠናከር የጀርመን የልማት ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የስልጠና ማዕከላት ግንባታና ግብዓቶችን የማሟላት ሥራዎች አከናውኗል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በልማት ድርጅቱ የተከናወኑ ሥራዎችን ዛሬ ጎብኝተዋል።

በእዚህ ወቅት አቶ ኡሞድ እንዳሉት ግብርና መር ኢኮኖሚውን ወደኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር እንደሀገር የተያዘውን ግብ ለማሳካት በኢንዱስትሪ ዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋል።

ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ኃላፊነት የላቀ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዘርፉ የሚፈልገውን የሰው ኃይል ከማፍራት ባለፈ ሥራ ፈጣሪ ትውልድ በመፈጠር የስራ አጥነትን በማቃለል በኩል ሚናቸው የጎላ መሆኑንም አቶ ኡሞድ ገልጸዋል።

በመሆኑም የጋምቤላ ኦፔኖ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የስልጠና አድማሱና ጥራቱን አጠናክሮ በማስቀጠል የተሰጡትን ተቋማዊ ተልዕኮዎች በብቃት ለመወጣት በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።

እንደ ርዕሰመስተዳድሩ ገለጻ ኮሌጁ ለጀመራቸው የሰው ኃብት ልማት ሥራዎች መሳካት የባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ሊጠናከር ይገባል።

የጀርመን የልማት ድርጅት የኮሌጁን አቅም ለማጠናከር ላደረገው የስልጠና ማዕከላት ግንባታና ግብዓት የማሟላት ሥራዎች ምስጋናም አቅርበዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።

የክልሉ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዊዋል ያት በበኩላቸው እንዳሉት፣ "የልማት ድርጅቱ የስልጠና ማዕከላት ግንባታ፣ እድሳትና ግብዓት የማሟላት ሥራዎች የኮሌጁን የስልጠና አቅም ያጠናክራሉ"።

በጀርመን የልማት ድርጅት (ጂ.አይ.ዜድ) የጋምቤላ ፕሮጀክት አስተባባሪ ታጃት ፓል የኮሌጁን የስልጠና አቅም ለማጠናከር ድርጅቱ የጀመራቸውን የአቅም ግንባታ ሥራዎች በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የልማት ድርጅቱ ከ16 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል የሦስት የስልጠና ማዕከላት እድሳትና ግንባታ፣ የኮሌጁ ዙሪያ አጥር ግንባታ ሥራ እንዲሁም የስልጠና ማሽነሪ ግብዓቶች ይገኙበታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም