በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ምጣኔ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ምጣኔ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገለጸ
ጥቅምት 18/2015 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ምጣኔ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱ ተገለጸ፡፡
የሀንዝ አማካሪ ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግሉ የጤና ዘርፍ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ላይ ያለውን ሚና በተመለከተ ያጠናውን ጥናት ይፋ አድርጓል።
ጥናቱን ያከናወነው የሀንዝ አማካሪ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዘላለም አዱኛ ባለፉት 20 ዓመታት የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ስራዎች ሲከናወኑ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚህም የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነት ከ20 ዓመት በፊት ከነበረበት 8 በመቶ ወደ 41 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
የመንግስት ጤና ተቋማት በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ 87 በመቶ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት፡፡
ቀሪው ድርሻ የግል የጤና ተቋማት መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የግሉ ሴክተር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቱን አማራጭና ተደራሽነት ይበልጥ እንዲሰፋ ሊደግፍ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ተደራሽነቱን ይበልጥ ለማስፋት የመንግስትና የግል ጤና ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም በጥናቱ ተመላክቷል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና እና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም መሰል ጥናቶች እንደ ሀገር በጤናው ዘርፍ የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት አጋዥ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የቤተሰብ ምጣኔ ዕቅድ አገልግሎት ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል እና የእናቶችና ህጻናት ሞት ለመቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ተደራሽነትን ወደ 54 በመቶ ከፍ ለማድረግ እቅድ መያዙን ጠቅሰው፤ በጥናቱ የተገኘውን ምክረ ሃሳብ እቅዱን ለማሳካት እንደ ግብዓት እንደሚጠቅም ተናግረዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ለመጠቀም ከሚፈልጉ ሴቶች መካከል 20 በመቶ የሚሆኑት በቤተሰብ፣ በጓደኛና በተለያዩ ጫናዎች አገልግሎቱን እያገኙ አለመሆኑን ተናግረዋል።