በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ በተሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠናከረ ምርመራ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢኮኖሚ አሻጥር ላይ በተሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠናከረ ምርመራ እየተደረገ ነው
ጥቅምት 18/2015 /ኢዜአ/ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና በሌሎች የኢኮኖሚ አሻጥሮች ላይ በተሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ የሚያስችል የተጠናከረ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የኢኮኖሚ አሻጥር ኢኮኖሚን በማዳከም በሀገርና መንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር እንዲሁም በአቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ህገ-ወጥ ቡድኖች የሚፈጥሩት ሴራ ነው፡፡
በተጨማሪ አሸባሪ ቡድኖች ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ለመግዛት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙበት ስልት መሆኑ ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታክቲክ ወንጀሎች ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ብርሀኑ አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢኮኖሚ አሻጥር ህገ-ወጥ ቡድኖች በመንግስትና ህዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚጠቀሙበት ድምጽ አልባ ጦርነት ነው፡፡
በኢትዮጵያ በተለይም ከለውጡ በኋላ በህገ ወጥ መንገድ መበልጸግ የሚፈልጉ ቡድኖች ግብር ለመሰወር በማሰብ አሊያም የሀገርን ኢኮኖሚ ለማዳከም በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እየተሳተፉ መሆኑን ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
በዚህም የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ከህብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማና በሚያከናውነው ጥልቅ ምርመራ አማካኝነት የውጭ ምንዛሬ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በማድረግና በህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ ጀምሯል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትና ከብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ባደረገው ምርምራ በህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር የተሳተፉ 25 ግለሰቦችና ድርጅቶች የሂሳብ አካውንት ታግዷል ብለዋል፡፡
ፖሊስ በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር በተሳተፉት ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ባደረገው ምርመራ የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ በህጋዊ መንገድ ከሚሰሩበት የችርቻሮ ንግድ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል ብለዋል፡፡
ለአብነት አንድ ተጠርጣሪ የችርቻሮ ንግድ እየሰራ በአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር ውስጥ ብቻ 15 የባንክ ሒሳብ ደብተር ከፍቶ 199 ሚሊዬን ብር ማንቀሳቀሱን በምርመራ ደርሰንበታል ብለዋል፡፡
ይሄም ገንዘቡ በህጋዊ ፈቃድ ከሚሰራው የችርቻሮ ንግድ አንጻር የተጋነነ ከመሆኑም በላይ የገንዘብ ዝውውሩ ያለ ንግድ እንቅስቃሴ የተፈጸመ እንደሆነም ተደርሶበታል ነው ያሉት፡፡
ፖሊስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በ25 ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይ ባደረገው ምርመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ አምስት ቢሊየን 115 ሚሊየን 814 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ያለ ግብይት ማንቀሳቀሳቸውን እንደደረሰበት ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በታገዱት የባንክ ሒሳቦች ከ135 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ መገኘቱንም አረጋግጠዋል፡፡
ድርጅቶቹና ግለሰቦቹ የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ ግብርን ለመሰወር የሚደረግ ህገ-ወጥ ተግባር ከመሆኑ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ በተደረገ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ የተገኘ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የሀገርን ኢኮኖሚ በማዳከም በመንግስትና ህዝብ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ህገ-ወጥ ተግባር የመከላከሉ ስራ ለፖሊስ ወይም ለተወሰኑ የጸጥታ ተቋማት ብቻ የሚሰጥ ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉንም ትብብር እንደሚጠይቅ መገንዘብ ይገባል ብለዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት፣ የፋይናነስ ደህንነት አገልግሎትና ከክልል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በተጠናከረ መልኩ በትብብር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ በማሳጣት ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ለማዳከም በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶና ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡