ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን አስታወቀ

ጥቅምት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱን አስታወቀ።

ከአገራዊ ለውጡ በፊት ባሉ ዓመታት ሙስና እና ብልሹ አሰራር በስፋት ተንሰራፍቶ ከነበረባቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ይጠቀሳል፡፡

በተለይ ባንኩ ይከተለው የነበረው የብድር አሰጣጥ እና አመላለስ ስርዓት ተቋሙን ለብልሹ አሰራር ያጋለጠ እንደነበር ነው የሚጠቀሰው፡፡

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባንኩ ተቋማዊ የለውጥ ስራዎችን በማከናወን ችግሮቹ እንዲቀረፉ የተለያዩ ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ በዚህም መሻሻሎች እየተመዘገቡ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የባንኩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዮሃንስ አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ባንኩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከዚህ ቀደም ከሰጠው ብድር ውስጥ 4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጻር 65 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ በሩብ ዓመቱ 4 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብድር ያፀደቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህም ውስጥ የአምራች ዘርፉ ከፍተኛውን የብድር ድርሻ እንደሚይዝ ተናግረዋል፡፡  

ባንኩ በሩብ ዓመቱ ለመስጠት ካጸደቀው የብድር መጠን ውስጥ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚሆኑን መስጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

ባንኩ አገልግሎቱን ቀልጣፋ ማድረጉና ተበዳሪዎች ውጤታማ ስራ ማከናወን እንዲችሉ ስልጠና መስጠቱ ለአፈፃፀሙ መሻሻል አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።

ባንኩ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገልግሎቱን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ ባደረገው ጥረት የተበላሸ ብድር እንዲቀንስ ማስቻሉንና በሩብ አመቱ የተበላሸ ብድር መጠን በ2014 በጀት አመት ከነበረበት 12 በመቶ ወደ 11 በመቶ መቀነሱን ተናግረዋል።

ባንኩ በሩብ አመቱ 740 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሩብ አዓመቱ አፈፃፀም ባንኩ በበጀት ዓመቱ የያዛቸውን እቅዶች ማሳካት እንደሚችል ያመላከተ እንደሆነም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም