ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት"በሀገር ልማትና ዕድገት ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ የጋራ አቋም አለው"

ሀዋሳ ጥቅምት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) "በሀገር ልማትና ዕድገት ጉዳይ ላይ ምክር ቤቱ የጋራ አቋም እንዳለው"  የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስታወቀ።

 ምክር ቤቱ ተቀራርቦ አብሮ የመስራት ባህልን በማጠናከር የኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴ በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባም አስታውቋል። 

የምክር ቤቱ አባላት በሲዳማ ክልል እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በአለታ ወንዶ፣ ሁላ እና ጭሮኔ ወረዳዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ ዓለሙ እንደተናገሩት፤ ጉብኝት የተደረገባቸው በሲዳማ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች በኩታገጠም እየተከናወኑ ያሉ የስንዴ፣ የቡናና መሰል የግብርና ልማት ሥራዎችም መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች አስደናቂ የልማት ሥራዎች እንደተከናወኑ ማየታቸውን የገለጹት ዶክተር መብራቱ፣ "ይህን አጠናክሮ ማስቀጠል ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የመቻል ራዕይዋን ከማሳካት የሚያግዳት የለም ብለዋል።

"በሀገር ልማትና ዕድገት ምክር ቤቱ የጋራ አቋም አለው" ያሉት ዶክተር መብራቱ፣ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ከዚህ ቀደም በመንግስትና በፓርቲዎች መካከል የነበረው መገፋፋት መወገዱን ገልጸዋል።

አሁን እየታየ ያለውን አብሮና ተቀራርቦ የመስራት ባህል በማጠናከር የኢትዮጵያን የልማት ግስጋሴ በዘላቂነት ማስቀጠል ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።

በጉብኝቱ ላይ ከተሳተፉ ፓርቲዎች መካከል ከካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ህብረት የመጡት አቶ ክፍሌ መሸሻ እንዳሉት፣ ከዚህ በፊት ከመንግስት ጋር ተባብሮ መስራት አልተለመደም ነበር።

በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች ባልተለመደ መልኩ በሀገር ልማት ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር እየተደረገ ባለው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

"በጋራ የመሥራት ባህሉ መጠናከር በሀገራችን ያሉ ጸጋዎች ከመረዳት ባለፈ ሀገራዊ የልማት ግቦችን ተረድተን የበኩላችንን አስተዋጾ ለመወጣት ያግዛናል" ብለዋል።

"ልማትና ሰላም የሁሉም የጋራ አጀንዳ ነው" ያሉት አቶ ክፍሌ፣ "በእነዚህ ጉዳዮች ተቀራርቦ በጋራ በመስራት ኢትዮጵያን አንድ እርምጃ ከፍ ለማድረግ እንሰራለን" ብለዋል።

የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ መዲና ከዳፎ በበኩላቸው፣ በሲዳማ ክልል ባዩት የግብርና ልማት ሥራዎች መገረማቸውን ገልጸዋል።

የሰብል ምርቱ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ እንደሀገር በጎበኟቸው የልማት ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ ማየታቸው ተስፋ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።  

"በተለይም በየአካባቢው ባዩት የስንዴና ሌሎች የልማት ሥራዎች ጠንክሮ ከተሠራ የማይቻል ነገር እንደሌለ ትምህርት ሰጥቶናል" ብለዋል።

"ሊለማ የሚችል ጸጋና ሀብት እንዲሁም መሥራት የሚችል ዕውቀትና ሰው ስላለን ከተሠራ በቀጣይ ልመና አይኖርም" ያሉት ወይዘሮ መዲና፣ "በሀገር ልማትና ሰላም አንድነትን ማጠናከር ከተቻለ ሁሉንም ማሳካት ይቻላል" ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የሲዳማ ክልል ጽህፈት ቤት የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ሃላፊ አቶ አስፋው ጎኖሶ፤ የምክር ቤቱ አበላት በክልሉ በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን የቡና፣ የስንዴ፣ ገብስና ሌሎች ሰብሎች መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት የተጀመሩ ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበባቸው መሆኑን በጉብኝቱ ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

"በተለይ ባልተለመደ ሁኔታ ቡናና ስንዴን በኩታ ገጠም ማሳ በማልማት ምርታማነትንና ጥራትን ለማሳደግ የተደረገው ጥረት ስኬታማ ነው" ብለዋል።

ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የተጀመረውን አብሮ የመሥራት ባህል ለማዳበር እያሳዩት ያለው መነሳሳት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አቶ አስፋው ገልጸዋል።

ጉብኝቱ በተደረገበት አለታ ወንዶ ወረዳ ወቶ ቀበሌ ቡና አምራች የሆኑት አርሶ አደር መስፍን ዘለቀ ሰባት ሆነው በ4 ሄክታር ማሳ ላይ በኩታ ገጠም ቡና እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእሳቸው ድርሻ 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት መሆኑን ጠቁመው፣ ከዚህም እስከ 100 ኩንታል ቡና ለማግኘት አቅደው እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በጭሮኔ ወረዳ ዳጋላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አበበ ቱሳኖ በበኩላቸው፤ በሦስት ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ እያለሙ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ለልማቱ ስኬታማነት የግብርና ባለሙያዎች ድጋፍና የግብአት አቅርቦት መልካም መሆኑን አቶ አበበ ገልጸው፤ ካለሙት መሬት ከ60 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የእርሻ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ክፍሌ ሻሾ በበኩላቸው፣ በመኸሩ ከ92 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህም ከ2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የጠቆሙት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም