ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር ያስችላል በሚል የፖለቲካ ስሌት የተቋቋመ ስብስብ ነው - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ


ጥቅምት 18 2015 (ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደር ያስችላል በሚል የፖለቲካ ስሌት የተቋቋመ ስብስብ ነው” ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።


“አንዳንድ አካላት በፖለቲካዊ ጫና እሳቤ በኢትዮጵያ የዳርፉር አይነት ታሪክ መፍጠር እንደሚፈልጉ በግልጽ በመናገር ላይ ናቸው” ብለዋል አምባሳደር ታዬ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ።


የኮሚሽኑ ሪፖርቶች ኢትዮጵያ ላይ ጨምሮ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ከፈጠራ ታሪክነት የዘለለ ትርጉም እንደሌላቸው አመልክተዋል።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያ ላይ የበረታ ጫና ማሳደር ያስችላል በሚል የፖለቲካ ስሌት የተቋቋመ ስብስብ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል ነው ያሉት ቋሚ መልዕክተኛው።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ባደረገው 51ኛ መደበኛ ስብሰባ የኮሚሽኑን የቆይታ ጊዜ በአንድ ዓመት ያራዘመ ቢሆንም ኢትዮጵያ የውሳኔ ሀሳቡን እንደማትቀበልና እንደምትቃወም መግለጿ ይታወቃል።

በቅርቡ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣውን የሰብአዊ መብት ሪፖርት መንግስት እንደማይቀበለው ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

ሪፖርቱ ከደረጃ በታች የሆነ፣ሙያዊ ይዘት የጎደለውና ግድ የለሽነት የተሞላበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት በሰብአዊ መብት ሽፋን ስም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን የማስፈጸም ተልዕኮ ያለው መሆኑንም መንግስት ለሪፖርቱ በሰጠው ምላሽ መግለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም