የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በየአካባቢው በማስፋፋት የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ መገንባት ይገባል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

94

ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችን በየአካባቢው በማስፋፋት የተሻለ ስብዕና ያለው ትውልድ መገንባት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በመዲናዋ አራዳ ክፍለ ከተማ በአዲስ መልክ የተገነባውን የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ መርቀው በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡

በተለምዶ "15 ሜዳ" ተብሎ የሚጠራው የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ ከዚህ ቀደም ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ምቹ አልነበረም።

በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በአዲስ መልኩ ተገንብቶ በመጠናቀቁ በዛሬው እለት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል ።

የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራው ግንባታ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚያመች መልኩ የተገነባ በመሆኑ የቀደመ አገልግሎቱን ይሰጣል።

የስፖርት ማዘውተሪያው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተመርቆ ሲከፈት ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችም ተገኝተዋል።

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራው ግንባታ የክረምት በጎ ፈቃድ ፕሮጀክት አካል መሆኑም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ለወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ በመገንባት የተሻለ ስብእና እንዲኖራቸው መስራት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎችን ጨምሮ ሌሎች አካላት ይህንን ተሞክሮ ማስፋት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ወጣቶች መልካም ነገር ማየት ይገባቸዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ የተሻለ ስብዕና ያላቸውን ወጣቶች መገንባት የሚያስችሉ ማእከላት ያስፈልጋሉ ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ በርካታ ተቋማት መገንባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ 9 ሚሊዮን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ለአብነት ያነሱት፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መስፋፋት ደግሞ ወጣቶች በተሻለ ስብእና ተገንብተው ለነገ አገር ተረካቢነት ብቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርጋቸው አንስተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በየአካባቢው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲስፋፋ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተሻለ አቅም ያላት አገር መሆኗን አንስተው፤ ይህን አቅም ለልማት ለማዋል ደግሞ ወጣቶችን ማብቃት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግስት በቴክኖሎጂና መልካም ስብዕና የተገነቡ አገር ተረካቢ ወጣቶችን ለማፍራት እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የበለጸገች ያደገችና የአፍሪካ ኩራት የሆነች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማስረከብ በትብብር መስራት አለብን ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ታዳጊ አማኑ ዩሀንስና ወጣት ኤሊያስ አብድረህማን በበኩላቸው የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራው ከዚህ ቀደም ለስፖርታዊ ጨዋታ ምቹ እንዳልነበር አንስተዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራው እንደ አዲስ እንዲገነባ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም