የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ይካሄዳል
ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ከፊታችን ቅዳሜ ጀምሮ ለሦሰት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ኮሚቴ ግብረ-ኃይል አስታወቀ።
የመጀመሪያው የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ "Integrated Africa the bridge of PM Abiy Ahmed" በሚል ሃሳብ ከጥቅምት 19 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ይካሄዳል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ከ50 በላይ አገራት የተውጣጡ ወጣት መሪዎች ይሳተፉበታል ተብሏል።
የጉባዔው ዓላማ የፓን-አፍሪካኒዝም እሳቤና ፍልስፍና ለአዲሱ የአፍሪካ ትውልድ ማስረጽና አብሮነትን ለማጠናከር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የአፍሪካ ወጣቶች ጉባዔ ኮሚቴ ግብረ-ኃይል ሰብሳቢ አለማየሁ ሰይፉ፤ ጉባዔውን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በጉባዔው የቀድሞ የአፍሪካ መሪዎች በፓን-አፍሪካኒዝም የነበራቸውን ሚና በተመለከተ ለማውሳት ቤተሰቦቻቸው እንዲገኙ የተጋበዙ መሆኑን ተናግረዋል።
በጉባኤው በአፍሪካ ትብብር እና ወንድማማችነት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የምርምር እና ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያሳዩ የተጠናቀቁ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጉብኝትም እንደሚኖር ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በጉባዔው ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉ ይሆናል።