በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው-ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው-ቢሮው
ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳባ ቱንጋ ገለጹ።
ከተለያዩ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያሉበትን የአፈፃጸም ደረጃ ጎብኝተዋል።
ጋዜጠኞቹም የታላቁ ቤተ-መንግስት የመኪና ማቆሚያ፣ የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር፣ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ማቋቋሚያ እና የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል የአፈፃጸም ደረጃን ጎብኝተዋል።
የታላቁ ቤተ-መንግስት የመኪና ማቆሚያ አምፊ ትያትር፣ ካፍቴሪያ፣ ሱቆችና ልዩ ልዩ ቢሮዎችን በመያዝ በ1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዳባ ቱንጋ፤ በመዲናዋ እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶች ገጽታን ከማሳደግ ባለፈ የነዋሪዎችን ህይወት የሚቀይሩና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በተያዘላቸው ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ምልከታ የተደረገበት የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር የግንባታ ሂደትም 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶችን፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ልዩ ልዩ ቢሮዎች እንዳሉት ተገልጿል።
በኮዬ ፈጬ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ማቋቋሚያ የእንስሳት እርባታ ማዕከል በልማት ለተነሱ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው ከሚፈጥረው የስራ እድል በተጨማሪ የመዲናዋን የኑሮ ውድነት በማቃለል ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተነግሯል።
የትራፊክ ማኔጅመንት ማዕከል ደግሞ 93 በመቶ የአፈፃጸም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ጤናማ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ጠይባ ሎና፤ በ2014 በጀት አመት ከ300 በላይ ግዙፍ፣ መካከለኛ እና አነስተኛ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው መጠናቀቁን አስታውሰዋል።
በዘንድሮው ዓመትም በርካታ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቶቹ ግንባታም በማጠናቀቂያ፣ በግንባታ እና በጅማሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ፕሮጀክቶቹም የከተማዋን ገጽታ በመቀየር በስራ እድል ፈጠራ፣ የዋጋ ንረትን በማረጋጋት እንዲሁም ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖዎችን በማቃለል ጉልህ ጠቀሜታ እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ ኃላፊዋ ኢንጂነር አያልነሽ ሀብተማርያም፤ የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማዕከል የአርሶ አደሩን ህይወት ለመቀየር ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጣል ብለዋል።
ማዕከሉ ውደ ስራ ሲገባም ለልማት ተነሺዎች የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በመዲናዋ የሚስተዋለውን የእንስሳት ስጋና ወተት ተዋጽኦ እጥረት ለማቃለል የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ሕጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤትም ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ አሟልቶ ግንባታው እየተጠናቀቀ ይገኛል ብለዋል።
የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ማቋቋሚያና የእንስሳት እርባታና ተዋጽኦ ማዕከል ከ300 በላይ ከብቶችን ለማድለብ፣ 300 የወተት ላሞችን እና 40 ሺህ ዶሮዎችን በተመሣሣይ ጊዜ ለማርባት የሚያስችሉ ሼዶች የተሟሉለት መሆኑም ተገልጿል።