የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዞን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ይሳተፋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዞን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ይሳተፋል
ጥቅምት 17/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የወንዶች እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ዞን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ይሳተፋል።
ከጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሱዳን አዘጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ዞን አፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር በሚመለከት የቡድኑ አሰልጣኝ እድሉ ደረጄ መግለጫ ሰጥተዋል።
ለውድድሩ የዝግጅት ጊዜ አጭር መሆኑን የገለጹት አሰልጣኙ እድሜና ችሎታቸውን መሰረት በማድረግ 23 ተጫዋቾች መመረጣቸውን ገልጸዋል።
የተጋጣሚ ቡድኖችን መረጃ ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ባሰቡት ልክ አለመሳካቱን ጠቅሰው፤ የተጫዋቾቻቸውን የማሸነፍ ስነ-ልቦና በመገንባት ጭምር ልምምድ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በሱዳን አዘጋጅነት በሚካሄደው የሴካፋ ዞን ከ20 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ኢትዮጵያ በምድብ ''ለ'' ከታንዛኒያ እና ዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር መደልደሉ ይታወቃል።
የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾችና የልዑካን ቡድኑ አባላት የፊታችን እሑድ ወደ ሱዳን ያቀናል ተብሎ ይጠበቃል።