የአሜሪካ ሆሎኮስት ሚሞሪያል ሙዚየም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ሀሰተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ ሆሎኮስት ሚሞሪያል ሙዚየም ኢትዮጵያን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ሀሰተኛ ነው
ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) የአሜሪካ ሆሎኮስት ሚሞሪያል ሙዚየም ኢትጵያን አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ሀላፊነት የጎደለውና የአሸባሪው ሕወሓት ቡድንን ፕሮፖጋንዳ ለማስተጋባት ያለመ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገለጸ።
ኤምባሲው ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሙዚየሙ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ያወጣው ዘገባ ከእውነት የራቀ ና ያለ ምንም ማስረጃ የተሰራ መሆኑን አመላክቷል።
ዘገባው አሸባሪ ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች ሲፈጽም የቆየውን በግፍ የተሞላ የጭካኔ ወንጀል ችላ በማለት ሀላፊነት በጎደለው መረጃ የተሰራ ነው ብሎታል ።
ኢትዮጵያ ህጋዊ የሆነ የሰበአዊ መብት ተቋም አላት ያለው ኤምባሲው ሙዚየሙ ከእውነት የራቁ ዘገባዎችን ከመስራቱ በፊት መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያሳይ፣ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ሚዛናዊ ማስረጃ ማሰባሰብ እንዳለበት አሳስቧል።
የኢትዮጵያ የሰበአዊ መብቶች ካውንስል እንዲሁም የተባበሩት መንግስታ ከፍተኛ የሰበአዊ መብት ኮሚሽነር ቡድን በትግራይ ክልል የጋራ ጥናት እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የኢትዮጵያ መንግስት ለሰበአዊ መብቶች መጠበቅ ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን አስታውሷል።
የጋራ ቡድኑ የጥናት ግኝት መሰረት በማድረግ በጥናቱ ላይ የተካተቱ የውሳኔ ሀሳቦች እንዲተገበሩና ግልጸኝነት የተሞላበት እርምጃ እንዲወሰድ የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሷል።
በአሁኑ ወቅትም ሰበአዊ እርዳታ በክልሉ ተደራሽ እንዲሆን ከተለያዩ ግብረ-ሠናይ ድርጅቶች ጋር በመስራት ላይ እንደሚገኝ በመጠቆም በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በመካሄድ ላይ ለሚገኘው የሰላም ንግግር ያለውን ቁርጠኝነት ገልጿል።
በመሆኑም ሙዚየሙ በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ በተለይም የጦርነቱን አጀማመር ትክክለኛ ምክንያት ለአንባብያኑ በማሳወቅ እውነተኛ ዘገባ መስራት እንዳለበት አሳስቧል።