በኢትዮጵያና ጂቡቲ መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ለአፍሪካ ቀንድና ለቀጣናው ጥሩ ተምሳሌት የሚሆን ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና ጂቡቲ መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ለአፍሪካ ቀንድና ለቀጣናው ጥሩ ተምሳሌት የሚሆን ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያና ጂቡቲ መካከል ያለው በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራና ታሪካዊ ግንኙነት ለአፍሪካ እና ለቀጣናው አገራት በጥሩ ተምሳሌትነት የሚወሰድ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።
እ.ኤ.አ በ1981 የተቋቋመው የኢትዮ-ጂቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን 16ኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ በማጠቃለያ መርሃ-ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት ኢትዮጵያና ጂቡቲ በብዙ መልኩ የተሳሰረና የተጋመደ ግንኙነትና ታሪክ አላቸው ብለዋል።
የኢትዮ-ጂቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በጋራ ስትራቴጂካዊና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ የቋንቋና የሕዝብ ለሕዝብ ጠንካራ ግንኙነት ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለቀጣናው አገራት በጥሩ ተምሳሌትነት የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገሮች መካከል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተው ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የጂቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር መሀመድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው፤ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
በንግድና ኢንቨስትመንት፣ ትራንስፖርት፣ ወደብና ትራንዚት አጠቃቀም፣ ጸጥታና ደኅንነት በሌሎችም የጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያና ጂቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ግዥ ስምምነት መፈራረማቸውን ገልጸው፤ ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት በጋራ የመልማት ፍላጎት ያሳያል ብለዋል።
በአዲስ አበባ በተካሄደው 16ኛው የኢትዮ-ጂቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች አፈጻጸም ግምገማና ያጋጠሙ ችግሮች የመፍትሔ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ እንደነበርም ተገልጿል፡፡