ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ የ11 ሀገራት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የዶሮ እና የእንስሳት ሀብት ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ተከፈተ

ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ጨምሮ የ11 ሀገራት ኩባንያዎች የሚሳተፉበት የዶሮ እና የእንስሳት ሀብት  ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

አውደ-ርዕዩ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን የማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠርን ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።

በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ዳዊት፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ፣ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ የግብርና አማካሪ ሚውስ ብሮወርና የተሳታፊ ኩባንያዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወንዳለ ሀብታሙ በዚሁ ወቅት፤ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የዶሮና የእንስሳት ሀብት በተገቢው ሁኔታ አልምታ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራች ነው ብለዋል።

የዛሬው አውደ ርዕይ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን የኢንቨስትመንት እድል ለባለሃብቶች ለማስተዋወቅና በዘርፉ ለተሰማሩትም የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶችም በአውደ ርዕዩ ከተሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የቴክኖሎጂና የእውቀት ልምድ ልውውጥ የሚያገኙበት መልካም አጋጣሚ መኖሩንም ጠቅሰዋል።

የእንስሳት ሀብትን በተደራጀና ዘመኑ በሚጠይቀው ቴክኖሎጂ በመታገዝ ለማልማትና የእንስሳት ተዋጽኦን በማቀነባበር ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

አቶ ወንዳለ አያይዘውም በአውደ ርዕዩ የእንስሳት መኖና የእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ጥሩ ልምድ የሚገኝበት ነው ብለዋል፡፡ 

የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያንና አዲስ አበባን መዳረሻ በማድረግ በርካታ ባዛሮች፣ ኮንፍረንሶችና አውደ ርዕዮች በመስተናገድ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ የተከፈተው አውደ ርዕይ ለገፅታ ግንባታና ለአውደ ርዕይ ቱሪዝም ካለው ሚና ባሻገር የሀገሪቱን እምቅ ሀብቶችን በማስተዋወቅ ባለሃብቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብ ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ጠቅሰዋል።

የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በወተት፣ ዶሮና የሥጋ ምርት የእሴት ሰንሰለት ላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና ልምድ ለመለዋወጥ እድል እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በአፍሪካ በሕዝብ ቁጥር ማደግና በከተሞች መስፋፋት የዶሮና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርት ፍላጎት በፍጥነት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ሆኖም በአህጉሪቱ ለዶሮና ለእንስሳት ሀብት ልማት የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ ባለው የገበያ ፍላጎት ልክ ማምረት እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት።

በመሆኑም መንግስታት ለዘርፉ ኢንቨስትመንት ማደግና የገበያውን ፍላጎት የሚያሟላ ምርት ማቅረብ እንዲቻል ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

አውደ-ርዕዩ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ክፍት ሲሆን ከ70 በላይ ኩባንያዎችም ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ይዘው ቀርበዋል።

ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም የወተትና የዶሮ ሀብት ልማት ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ውይይት እና ሥልጠና እንደሚካሄድም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም