የፕላዝማ ትምህርት ማስተላለፊያ መሳሪያ ስራ ሳይጀምር ለብልሽት እየተዳረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፕላዝማ ትምህርት ማስተላለፊያ መሳሪያ ስራ ሳይጀምር ለብልሽት እየተዳረገ ነው
አምቦ መስከረም 14/2011 በምዕራብ ሸዋ ዞን ሊበን ጃዊ ወረዳ ከስምንት ዓመታት በፊት የተተከለው የፕላዝማ ትምህርት ማስተላለፊያ መሳሪያ አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን በወረዳው የባቢች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ገለጹ። የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ተሾመ ከበደ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ በፕላዝማ የሚተላለፈውን ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ተማሪዎች እኩል የመወዳደር እድል እንዲያገኙ ታስቦ መሳሪያው የተተከለው በ2002 ዓ.ም. ነበር ። የፕላዝማ ትምህርት ማስተላለፊያ መሳሪያው ከተተከለ ስምንት ዓመታት ቢያልፈውም በመብራት ችግር ምክንያት አገልግሎት መስጠት ሳይጀምር ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን አስረድተዋል ። የመብራት አገልግሎቱን ለማግኘት 297 ሺህ ብር ለኤሌክትሪክ አገልግሎት መስሪያ ቤት መከፈሉን ጠቁመው ሆኖም እስካሁን አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልተቻለ ርዕሰ መምህሩ ተናግረዋል ። በዚህም ምክንያት ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ትምህርት ባለማግኘታቸው በውጤታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የትምህርት ቤቱ የፊዚክስ መምህር አቶ ጋዲሣ ኢቲቻ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ መብራት አለመኖር ከፕላዝማ ትምህርቱ በተጨማሪ ተማሪዎች የኮምፒውተር ትምህርት የሚከታተሉበት እድል ማጣታቸውን አመልክተዋል፡፡ በትምህርት ቤቱ ለፈተና ማባዣ ተብለው የተገዙ መሳሪያዎችም በዚሁ ችግር ምክንያት ያለ አገልግሎት እንዲቀመጡ ተደርጓል ። አቶ ስዩም ጅክሳ የተባሉ የባቢች ከተማ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት ልጆቻችን በፕላዝማ እኩል የመማር እድል ስለማያገኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ ብሄራዊ ፈተናዎች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው ነው" ብለዋል ። ትምህርት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ተነጋግሮ የትምህርት ቤቱን የኤሌክትሪክ መብራት ችግር በአፋጣኝ መፍታት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በምዕራብ አዲስ አበባ ሪጅን የጨልያ ዲስትሪክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻምበል ከራ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በትራንስፎርመር እጥረት ምክንያት ችግሩ እንደተፈጠረ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዕቃው ተገዝቶ በቦታው በመድረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የትምህርት ቤቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግሩ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡