በሃዋሳ በዓሉንና ጉባኤዎቹን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ ዝግጀት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሃዋሳ በዓሉንና ጉባኤዎቹን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማስተናገድ ዝግጀት እየተደረገ ነው
ሀዋሳ መስከረም 14/2011 የመስቀል በዓልን ጨምሮ በሃዋሳ ከተማ የሚካሄዱ የደኢህዴንና ኢህአዴግ ጉባኤዎች ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከናወኑ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ ከ30 በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያካሄደባቸው መሆኑንም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል፡፡ ኮሚሽነሩ ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት የመስቀል ደመራ በዓልና የደኢህዴንና ኢህአዴግ ጉባኤዎች ያለእንከን መከናወን እንዲችሉ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ነው፡፡ "እነዚህ ኩነቶች እንዲደናቀፉ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ደርሰንበታል" ያሉት ኮሚሽነሩ ጉባኤዎቹ እንዳይሳኩ ለማድረግ ከሌሎች ክልል ወደ ክልሉ /ወደ ሃዋሳ ከተማ ገብተው የነበሩ 23 ፀጉረ ልውጥ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥራ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ በሃዋሳ ከተማ ህዝብ ላይም አለመረጋጋት ለመፍጠር ጨለማን ተገን አድርገው ድምፅ የሌላቸውን ስለታማ መሳሪያዎችን በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ስምንት ግለሰቦችን መያዛቸውንም አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቋሚና ድንገተኛ የኬላ ፍተሻዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፣ በእዚህም ሦስት ሽጉጦችና 300 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ተይዞ የምርመራ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ የህዝብና የሀገር ሰላም በማይፈልጉ ግለሰቦች የሽብር አሉባልታዎች በከተማው መሰራጨታቸውን ገልጸው የከተማው ህብረተሰብ እንደወትሮው ከፖሊስ ጎን በመቆም ደህንነቱን ይበልጥ እንዲያስጠብቅ ጠይቀዋል፡፡ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡ በ0462-21-28-70 እና 0462-20-18-87 የቋሚ ኮማንድ ፖስት መስመር ጥቆማና መረጃ መስጠት እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡ " 0462-20-10-46 እና 0912-68-76-71 የስልክ መስመሮችም ለከተማ ፖሊስ ማንኛውንም ጥቆማና መረጃ የሚቀበሉ ናቸው" ብለዋል። ሰላም እንዳይደፈርስ፣ የሁለቱም ድርጅቶች ጉባኤዎች ያለእንከን እንዲካሄዱና የመስቀል በዓል ሰላማዊ በሆነ መንገድ በድምቀት እንዲከበር የክልሉ ፖሊስ ፣ ልዩ ኃይልና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ጥምረት ፈጥረው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ የክልሉ ፖሊስ ከኦሮሚያ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ከሃዋሳ እስከ ሞጆ ድረስ ፖሊሳዊ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የደኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ከመስከረም 18 እስከ 21 የሚከበር ሲሆን ከመስከረም 23 እስከ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የኢህአዴግ ጉባኤ በሃዋሳ ከተማ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡