በኢንዱስትሪው የታየውን መነቃቃት በብቁ የሰው ኃይል መምራት ያስፈልጋል- ባለሙያዎች

65
አዲስ አበባ ግንቦት 11/2010 በኢንዱስትሪ ዘርፍ የታየውን ለውጥ በብቁ የሰው ኃይል በመምራትና ተፈላጊና ተወዳዳሪ ምርቶችን በማምረት የኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀጣይነት እንዲኖረው መሰራት አለበት ሲሉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ተናገሩ። ባለፈው በጀት ዓመት የማምረቻ ኢንዱስትሪው በ17 ነጥብ 4 በመቶ በማደግ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 6 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ መንግስት የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ዘርፉን ለማሳደግ የወሰደው የፖሊሲ አማራጭ መልካም መሆኑ ባለሙያዎችን ያስማማል። ባለሙዎቹ እነደሚሉት ግን የተወሰዱ አማራጮችን በብቁ የሰው ኃይል በመምራትና የዕውቀት ሽግግሩን በሚፈለገው ፍጥነት በማመቻቸት ግብርና መር  ኢኮኖሚውን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር የሚደረገውን ጥረት ማፋጠን ይገባል። በአገር ውስጥ የሚወጡ የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የመጠቀም ልምዱ መዳበርና ማደግ እንደሚኖርበትም ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ የሚመክሩት፡፡ የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ካሳ ተሻገር እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተመዘገበውን ተከታታይ ዕድገትና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የታየውን ለውጥ ለማስቀጠል የገበያ ተወዳዳሪነትን የማሳደግና የሰው ሃይሉን የማብቃቱ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡ በግብርና ምርቶች በተለይም በቡና፣ ሰሊጥ፣ አበባና በተወሰኑ ምርቶች ተወስኖ ያለው የወጪ ንግድ ዕድገት እያስመዘገበ ቢሆንም ቀጣይነት ላለው የኢኮኖሚ እድገት አዋጭ አይደለም የሚል ሃሳብም ሰንዝረዋል፡፡ ኤክስፖርት መር የሆኑ ምርቶችን ማምረትና ከውጭ ወደአገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለሚተኩት ትኩረት መስጠትም  ተጨማሪ እርምጃዎች መሆናቸውን  ሌላኛው ባለሙያ ዶክተር ለማ ጉዲሳ ተናግረዋል። እርምጃዎቹ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ከማስቀረት አልፎ ተጨማሪ ገቢ የሚያስገኙ በመሆኑ ለኢኮኖሚ ዕድገቱ ቀጣይነት መደላድል እንደሚፈጥር ነው ባለሙያው የገለጹት። ባለሙያው እንዳሉት ኢትዮጵያ ሰፊ የገበያ አማራጭ ያላት በመሆኑ በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ላይ እሴት ጨምሮ በጥራትና በብዛት ለዓለም ገበያ ማቅረብ ዋሳኝ ነው ። የተጀመረውን ልማት በአይነት፣ በብዛትና በጥራት ማስፋፋትና ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኢኮኖሚው በ2009 በጀት ዓመት የ10 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን በተለይም በበጀት ዓመቱ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የ18 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው ነበር የተተነበየው። የኢንዱስትሪው ክፍለ-ኢኮኖሚ በ18 ነጥብ 7 በመቶ በማደግ በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው የ10 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት የ4 ነጥብ 4 መቶኛ ነጥብ አስተዋጽኦ በማበርከት ከፍተኛውን ድርሻ መያዙን የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም