ቀጥታ፡

በአማራ ክልል በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የጂብሰም ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

ደጀን፣ ጥቅምት 17/2015(ኢዜአ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በደጀን ከተማ በ1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውን ታይም የጂብሰም ፋብሪካ መርቀው ስራ አስጀመሩ።

ርዕሰ መስተዳደሩና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በምስራቅ ጎጃም ዞን የሰብል ልማትን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን እየጎበኙ ይገኛሉ።

ከጉብኝታቸው ጎን ለጎን ነው ርእሰ መስተዳድሩ የጂብሰም ፋብሪካውን መርቀው ስራ ያስጀመሩት።

ፋብሪካውን ያስገነባው የበልስቲ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወስነ የግል ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ምህረቱ እንዳሉት ፋብሪካው በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ግንባታውንና የማሽን ተከላውን በማጠናቀቅ ወደ ማምረት ገብቷል።

ባለፈው ዓመት የካቲት ወር 2014 ዓ.ም የሙከራ ምርት መጀመሩን አስታውስው፤ አሁን ላይ የሙከራ ስራውን አጠናቆ በየቀኑ 500 ቶን ጂብሰም በማምረት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

በአንድ ቢሊዮን ወጪ የተገነባው የጂብሰም ፋብሪካው ለ214 ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠሩንና የፋብሪካው ምርት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለመደገፍ የጎላ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የፋብሪካውን የማምረት አቅም በቀን ወደ አንድ ሺህ ቶን ለማሳደግ የሚያስችለውን 2ኛው ምእራፍ ግንባታንም ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

በርእስ መስተዳድሩ የሚመራው የከፍተኛ አመራር ቡድን ማምሻውን በምስራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን ወረዳ በክላስተር የለማ የስንዴ ሰብል ይጎበኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም