ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለማሰለፍ ተቋማት ለምርትና አገልግሎት ጥራት ትኩረት ሊሰጡ ይገባል--ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና

ጥቅምት 17/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ ተቋማት ለምርትና አገልግሎት ጥራት ትኩረት በመስጠት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና ገለጹ

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሀና 9ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማትን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ በምርት፣ በአገልግሎት፣ በትምህርትና ጤና፣ በግንባታ የተሰማሩ ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶች ለጥራት ሽልማቱ ለውድድር ይቀርባሉ።

ተቋማቱ በዓለምአቀፍ መለኪያዎች መወዳደራቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህም ባለፈ በመስክ ምልከታ ዝርዝር ግምገማ መደረጉን ጠቁመዋል።

ውድድሩ አገልግሎቶች ጥራታቸው እንዲጨምር እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።

የሽልማት መርሃ-ግብሩ የፊታችን ቅዳሜ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በታላቁ ቤተመንግስት እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ጥራት ያለው ምርትና አገልግሎት ኢትዮጵያ መካከላኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ በመሆኑ ተቋማት ለጥራት ተኩረት መስጠት እንዳለባቸው አንስተዋል።

ከዚህ ባለፈም ምርትና አገልግሎቶች የደንበኞችን እርካታ የሚያሳድጉ መሆን እንዳለባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት በጥራት ስራ አመራር የላቀ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋማት እና ድርጅቶችን መሸለም፣ እንዲሁም ግለሰቦችና እና ተቋማት ጥራትን ባህል እንዲያደርጉ የስርጸት ስራ ማከናወን የድርጅቱ ዓላማዎች ናቸው ብለዋል።

በዘጠነኛው ዙር የጥራት ውድድር 45 የሚሆኑ ድርጅቶች ተመዝግበው 40ዎቹ እስከውድድሩ መጨረሻ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ለመጨረሻ ውድድር የደረሱት ተቋማት የፊታችን ቅዳሜ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ሽልማት እንደሚበረከትላቸው ጠቁመዋል።

በፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂነት የሚመራው የኢትዮጵያ ጥራትና ሽልማት ድርጅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዋልታ ሚድያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ጥምረት በ2000 ዓ.ም ተቋቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም