በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት ነው-- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት ነው-- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
ጥቅምት 17 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን የመጠገን ሥራ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገበት መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በሰሜኑ ጦርነት አሸባሪው ህወሓት በተለይም መሰረተ-ልማቶችን የማውደምና የመዝረፍ ሥራ በመፈፀሙ ከፍተኛ ኪሳራ አስከትሏል።
በተለይም በአማራና ትግራይ ክልሎች በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በማውደሙ የመብራት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም ጉዳትና ውድመት የደረሰበትን መሰረተ-ልማት በመጠገን ዳግም አገልግሎት ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰቆጣ፣ ላልይበላና ዋግኸምራ በጦርነቱ ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም ለማስጀመር ጥገና የተጀመረ ሲሆን ከአላማጣ ቆቦ እና ከአላማጣ ላልይበላ ያለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና በአንድ ሳምንት ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል።
ከባህርዳር–አላማጣ የተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መሥመር እስኪጠገን ድረስም ከኮምቦልቻ–አላማጣ ያለውን ባለ 230 ኪሎ ቮልት መሥመር የመጠገን ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል።
በመሆኑም በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በመጠገን የኃይል አገልግሎቱን ለማስጀመር ከፍተኛ ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በወልዲያ አላማጣ በኩል ያለው መስመር የጥገና ሥራ እየተከናወነ ሲሆን በወልቃይት ሑመራ እስከ ሽሬ ያለው መስመር ደግሞ የደረሰው ጉዳት መጠን ከታወቀ በኋላ የጥገና ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን በመጠገን ተቋርጦ የቆየውን የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም የማስጀመር ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ከአሸባሪው ህወሓት ነጻ በወጡ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስጀመር በጥናት ላይ የተመሰረተ ሥራ ቀደም ብሎ መጀመሩ ይታወቃል።