ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ቡና አምራቹ ለቡና ጥራት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል

ጅማ ፣ጥቅምት 17/2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ቡና አምራቹ ለቡና ጥራት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ።

በጅማ ከተማ "የቡና ምርት ጥራት ለዘላቂ እድገት" በሚል መሪ ቃል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አገራዊ ንቅናቄ ተካሂዷል።

የባለስልጣኑ ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የቡና ምርት መጠኑን ማሳደግ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጥራቱ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ደረጃውን የጠበቀ ምርት መሰብሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ይሆናል አምራቹም የተሻለ ገቢ ማግኘት ይችላል ብለዋል።

ዶክተር አዱኛ አክለውም በዘንድሮ አመት በአለም የቡና ገበያ የዋጋ መቀነስ እየታየ እንደሆነ ገልጸው ጥራት ያለውና ተወዳዳሪ ቡና ማቅረብ ይጠበቃል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አቦሴ በበኩላቸው የቡና ጥራትን ከሚቀንሱ ተግባራት መካከል በዋናነት በአምራቹ ዘንድ ለቡና ጥራት የሚሰጠው ትኩረት ያነሰ መሆኑ ነው ይላሉ።

ቡና ሳይቀላ አረንጓዴውን መልቀም፣ በንጹህ እቃ ያለመልቀም፣ ከረገፈ በኋላ ከመሬት መልቀም፣ የደረቀን ቡና ለገበያ ሲባል በውሃ ማርጠብና ሌሎች ችግሮች የቡናን ጥራት እያጓደሉ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ ለገበያ ማቅረብ፣ ንጽህናው ባልተጠበቀ ስፍራ ማከማቸትና ማጠራቀም እንዲሁም መሬት ላይ ማድረቅ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የቡና አምራች አርሶ አደሮች ለምርቱ ጥራት ልዩ ትኩረት መስጠት አለባቸው ያሉት አቶ ተስፋዬ የቡና ነጋዴዎችም የምርቱን ጥራት በሚገባ እያዩ መግዛት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የጅማ ቡና አምራች ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ዋናው መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የጅማ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ የሱፍ ሻሮ ናቸው።

በዞኑ ጥሩ ምርት የሚሰጥ የተሻለ የቡና ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ጥራቱን ለማሳደግ የግንዛቤ ማሳደግ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጎማ ወረዳ ግንባር ቀደም ቡና አምራች አርሶ አደር አቶ አብዱረህማን ፈድሉ እንዳሉት የሚሰበሰቡትን የቡና ምርት በጥራት እንደሚይዙ ገልጸው በዚህም ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም በአርሶ አደሩ ዘንድ ለጥራት ትኩረት የማይሰጠው በመሆኑ የባለሙያ ምክርና እገዛ ቢሰጥ ጥራቱ የተሻለ ይሆናል ብለዋል።

የንቅናቄ መድረኩ በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አዘጋጅነት የተከናወነ ሲሆን  ከፌዴራል፣ ከክልል፣ ከዞን እና ወረዳዎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም