በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ከ143 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከለማው መሬት ከ143 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል-ዶክተር ይልቃል ከፋለ
ምስራቅ ጎጃም (ኢዜአ) ጥቅምት 17/2015 በአማራ ክልል በመኸር ወቅት ከለማው 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ143 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለፁ።
በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የከፍተኛ አመራር ቡድን በምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የጤፍ ሰብልን ጎብኝቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት የመኸሩ ሰብል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።
በተለይም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች 12 የሰብል አይነቶችን በኩታ ገጠም ማልማት እንደተቻለም ገልፀዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግም አርሶ አደሩ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና አሠራሮችን እንዲተገብር የተጠናከረ የባለሙያና የአመራር ድጋፍ መሰጠቱም ርዕስ መስተዳደሩ አስታውሰዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሀይለማርያም ከፍያለው በበኩላቸው "በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ ተሰርቷል" ብለዋል።
"አርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂን እንዲጠቀም ከማድረግ ባለፈ በቂ ግብዓት እንዲቀርብ በመደረጉ የመኽር ሰብል ቁመና የታሰበውን ምርት ማግኘት በሚያስችል ደረጃ ላይ ይገኛል" ብለዋል።
በመኸር ወቅቱ የተለያዩ ሰብሎችን በ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ማልማት የተቻለ ሲሆን ይህም ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ሚና አለው።
በኩታ ገጠም ከለማው መሬት ከ64 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ሃላፊው አስታውቀዋል።