የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስንዴ ምርትን ማገበያየት ሊጀምር ነው

ጥቅምት 17/2015 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተያዘው ዓመት የስንዴ ምርትን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማገበያየት መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ እራሷን ለመቻል ከፍተኛ ትኩረት ከሰጠቻቸው የግብርና ልማት ሥራዎች አንዱ የስንዴ ምርት ነው።

የስንዴ ምርትን ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደ ሌሎች አገሮችም የመላክ አቅም እንዳለ በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወቃል።

አሁን ላይ ኬንያና ጂቡቲን ጨምሮ ሌሎች አገሮችም ከኢትዮጵያ ስንዴ የመሸመት ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀዋል።

በመሆኑም የስንዴ ምርትን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማገበያየት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ነጻነት ተስፋዬ በተለይ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የስንዴ ምርትን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት የሚያስችል ዝግጅት የተደረገ በመሆኑ በተያዘው ዓመት ማገበያየት ይጀመራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ15 ዓመት በፊት ምርቶችን ማገበያየት የጀመረው በበቆሎና ስንዴ ቢሆንም የስንዴ ምርታማነት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ከወራት ያለፈ ዕድሜ እንዳልነበረው አውስተዋል።

በአሁኑ ወቅት መንግሥት በስንዴ ምርት ላይ እያከናወነ ያለው ተግባር ምርትና ምርታማነቱ እንዲሁም የገበያ መዳረሻው እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

ምርት ገበያው ስንዴን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ማገበያየት የሚያስችለውን ረቂቅ ውል ያዘጋጀ ሲሆን ውሉን በማፅደቅ በዚህ ዓመት ምርቱን ማገበያየት ይጀምራል ብለዋል።

በምርት ገበያ ሥርዓት ማገበያየት የምርት ጥራትንና ብዛትን የበለጠ በማሳደግ የግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊ  የክፍያና የርክክብ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስችልም አስገንዝበዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ፣ አቅራቢውና ላኪው በአጠቃላይ አገር ማግኘት ያለባትን ጠቀሜታና የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

የስንዴ ምርት በግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባቱ የስንዴ ዋጋ የየዕለት መረጃ በቀላሉ ማግኘት ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል።

ምርት ገበያው ባሉት 25 ቅርንጫፎች አብዛኞቹ ከፍተኛ ስንዴ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ በመሆኑ አርሶ አደሩና አቅራቢው በቀላሉ ምርቱን ማስረከብ የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሩና አቅራቢው ምርቱን ወደ ምርት ገበያ ሲያመጣ ተፈትሾ ደረጃ ከተሰጠው በኋላ የአጭር ጊዜ ብድር ማግኘት የሚያስችለውን የመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋቱንም ገልጸዋል።

ይህም የስንዴ አቅራቢዎችንና አምራቾችን የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።

በተመሳሳይም ምርት ገበያው የእጣን፣ የኮረሪማ፣ የሩዝና የግብጦ ምርቶችን በዚህ ዓመት ማገበያየት እንደሚጀምርም አቶ ነጻነት ተስፋዬ ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም