በዞኑ የደረሰውን ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ 150 ኮምባይነር አሰማርተናል-ዞኑ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የደረሰውን ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ 150 ኮምባይነር አሰማርተናል-ዞኑ
አዳማ፤ ኢዜአ ጥቅምት 17 ቀን 2015 በዞኑ የደረሰውን ሰብል በወቅቱ ለመሰብሰብ 150 ኮምባይነር ማሰማራቱን የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ ለኢዜአ እንደገለፁት በ2014/15 የምርት ዘመን ከ4 መቶ 39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል።
በዞኑ የደረሰውን ሰብል ለመሰብሰብ 150 ኮምባይነር ለአጨዳ መሰማራቱን የገለፁት አቶ መስፍን እስካሁን 150 ሺህ ሄክታር ላይ ያለውን የስንዴና የጤፍ ሰብል ማንሳት መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥ 254 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ በኩታገጠም የተዘራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይ አዳሚቱሉ፣ ዱግዳ፣ ቦራ፣ ሊበን ጭቋላ፣ ሉሜ፣ አዳማ፣ ቦሰት፣ ፋንታሌና አደአ ወረዳዎች ሰብል የመሰብሰብ ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዋናነት የደረሰው ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀው ዝናብ እንዳይበላሽ ፈጥኖ ማንሳት ላይ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክቷል።
በዞኑ ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ያሉት አቶ መስፍን በኩታ ገጠም ከለማው የስንዴ ማሳ ላይ ከ6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ብለዋል።
በዞኑ ከመኸር እርሻ ብቻ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ሕገ ወጦች ሳይገቡበት በሕብረት ስራ ማሕበራት በኩል ለውጭ ገበያ እንዲያልፍ ይደረጋል ብለዋል።
በተለይ የምርት ብክነት እንዳይኖርና በተመሳሳይ ወቅት የምርቱን ጥራት በጠበቀ መልኩ ለማንሳት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዱግዳ ወረዳ አርሶ አደር ጉዴ ቆንዳሌ በበኩላቸው ''በኩታ ገጠም ማልማት የጀመርነው ቅርብ ጊዜ ነው፤ ድሮ በቆሎና ቦሎቄ ነበር የምንዘራው'' ብለዋል።
''የተሰጠን የስንዴ ምርጥ ዘር በ96 ቀን የሚደርስና በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ምርት የሚሰጥ ነው'' በማለት ይገልጻሉ።
ከሄክታር በአማካይ ከ28 እስከ 32 ኩንታል እያገኙ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ በአዳሚ ቱሉ ወረዳ አርሶ አደር ሮባ ሻንቆ ናቸው።
''በኩታ ገጠም በማልማታችን የተሻለ ምርት ከማግኘት ባለፈ ምርቱን በኮምፓይነር ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ በአንዴ እያነሱ ነው'' ብለዋል።